አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በኢኮኖሚ ረገድ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስርት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት 2011 ዓ.ም የተጀመረው ይህ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን በመጨመር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሬ፣ በምግብ ሉዓላዊነት ራስን በመቻል እና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያረከተ ይገኛል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከሚተከሉት ችግኞች መካከል እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ እና ማንጎ የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት ቡና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተከለ ሲሆን በውጤቱም ከፍተኛ እምርታ ተመዝግቦበታል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የቡና ምርት በመጠን እና በጥራት መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አመልክተዋል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት ዓመታዊ የቡና ምርት 550 ሺህ ሜትሪክ ቶን ብቻ ነበር፤ ይህ ቁጥር በ2018 ዓ.ም በሦስት እጥፍ አድጎ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማምረት ተችሏል፡፡
በ2018 ዓ.ም ብቻ ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ በ2014 ዓ.ም ተመዝግቦ ከነበረው 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ማደጉን ያሳያል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ 16 በመቶ የሚሆነውን የቡና ተክል ይሸፍናል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉት የቡና ችግኞች ሙሉ ለሙሉ ምርት መስጠት ሲጀምሩ ኢትዮጵያ አሁን በዓለም ቡና አምራችነት ካለችበት 5ኛ ደረጃ ወደ 3ኛ ብሎም 2ኛ ከፍ እንድትል ያስችላታል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ቡናን እንደ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ተክል ተወስዶ በመሰራቱ በአጭር ጊዜ የምርት መጠን እና ጥራትን በመጨመር የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ያለመ ትልቅ ብሔራዊ ፕሮግራም ሆኗል።
በቴዎድሮስ ሳህለ