ግብፅ በዚህ በሰለጠነው ዓለም የቅኝ ዘመን የውኃዎች የፖለቲካ የበላይነት እንዲነካባት አትፈልግም፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያ ከምድሯ እንኳን የሚፈልቁ የውኃ ሃብቶቿን አይደለም አልምታ መጠቀም በትኩረት እንኳን እንድታይ አትሻም፡፡
ሀገሪቷ ቀድሞ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ የውኃ ሃብቶቿን አቅዳ እንዳታለማ ስታደርግ ኖራለች፡፡
የሕዳሴ ግድብ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ግብፅ መሰናክሎችን ስታስቀምጥ ነው የቆየችው፡፡
ኢትዮጵያ ግን የነበሩ ችግሮችን ብትረዳም በፍትሃዊ መንገድ በመጠቀም በጋራ መልማትን ስታቀነቅን ቆይታለች፡፡
ግብፅ ሕዳሴው ተጠናቅቆ ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ከጭለማ ሲያወጣና ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ተጠቃሚ ሲያደርግ አሁንም የኢፍትሃዊነት ጩኸቷን አላቋረጠችም፡፡
ኢትዮጵያ ሌሎች የውኃ ሃብቶችን ማልማትና መጠቀም እንደማትችል አጀንዳ ማድረጓን ቀጥላለች፡፡
የግብፅ የዘመናት ማላዘን ሲታይ ዓባይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ በሱዳን በኩል ወደ እሷ የሚሄድ የማይመስላት ታደርገዋለች፡፡
ግብፅ ከቀድሞው ቅኝ ገዢዎች ስምምነት በመነሳት አሁንም የውኃው ብቸኛ ባለቤት ለመሆን ትፈልጋለች።
የኢትዮጵያ ጥያቄ ግን ዘወትር የጋራ ተጠቃሚነትና የፍትሃዊነት መርህ ነው፡፡
የሕዳሴ ግድብም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የተፈጥሮ ሃብትን ተጠቅሞ የመልማት ፍላጎትና ትጋት ህዝብን ከድህነት ለማውጣት ያለመ ፍትሃዊ እሳቤና ተግባር ነው።
ኢትዮጵያ ስለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዘወትር ብታቀነቅንም ግብፅ ግን በየዓመቱ ከዓባይ ወንዝ ከምታገኘው ግዙፍ የውኃ ድርሻ ከፍተኛውን መቶኛ በበረሃ ላይ በትነት ታባክናለች።
ሀገሪቷ በየዓመቱ በአማካይ ከ12 እስከ 17 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የዓባይ ውኃን በሰሃራ በረሃ ላይ በሚገኙ ግድቦችና ሰው ሰራሽ ሐይቆች አማካኝነት በትነት ታባክናለች።
ይህ የሚባክነው የውኃ መጠን ግብፅ በአጠቃላይ ከናይል ወንዝ የምታገኘውን ዓመታዊ ድርሻ (55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር) ከ20 በመቶ እስከ 30 በመቶ ይሸፍናል።
ይህ ግዙፍ የውኃ ብክነት ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል የአስዋንና የናስር ሐይቅ፣ የቶሽካ ፕሮጀክት፣ አዲሱ ዴልታና የበረሃ መስኖ ፕሮጀክቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ግብፅ በአስዋን ከፍተኛ ግድብ እና በናስር ሐይቅ ላይም መጠነ ሰፊ የውኃ ሃብት እያባከነች ነው፡፡
ሀገሪቷ ውኃውን በበረሃ መካከል በገነባችው ናስር ሐይቅ ላይ በማሰሯ ምክንያት፣ በሰሃራ በረሃ እጅግ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ሳቢያ በየዓመቱ ብቻውን ከ10 እስከ 14 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በአየር ላይ በትነት ያጠፋል።
ይህ መጠን ኢትዮጵያ በዓመት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት ከምትጠቀመው ውኃ ጋር ሊመጣጠን የሚችል ነው።
በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ግብፅ የአስዋን ግድብ እንዳይሞላ እና የተረፈውን ውኃ ለመቀልበስ በበረሃማ ቦታዎች ላይ የቶሽካ ሰው ሰራሽ ሐይቆችን ፈጥራለች።
በዚህ እጅግ ደረቅ ቀጣና ውስጥ ውኃው ለሰብል ልማት ሳይውል በዓመት እስከ 2.5 ሜትር ጥልቀት ያለው ውኃ በቀጥታ በትነትና ወደ መሬት በመስረግ ብቻ መክኖ ይቀራል።
ይህም በየዓመቱ ተጨማሪ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ያባክናል።
ግብፅ በአዲሱ ዴልታ እና የበረሃ መስኖ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መጠን ያለውን የውኃ ሃብት ታባክናለች፡፡
ሀገሪቷ የአባይን ውኃ በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርዝመት ባላቸው ክፍት ቦዮች በመሳብ ወደ ምዕራባዊው የሰሃራ በረሃ ትወስዳለች።
ውኃው ክፍት በሆኑ ቦዮች ላይ በረጅም ርቀት ሲጓዝ እና በበረሃው ጽኑ ፀሐይ ላይ በሚረጩ የመስኖ ሥራዎች አማካኝነት ሰብሎችን ለማርካት በሚሞከርበት ጊዜ ከፍተኛው መጠን አየር ላይ በትነት ይጠፋል።
ግብፅ ከምትፈጽመው የውኃ ትነት በተጨማሪ በግብርና ሥራ በምታለማቸው የተሳሳተ የዕፅዋት ምርጫ ምክንያት ከፍተኛ የውኃ ሃብት ታባክናለች፡፡
ሀገሪቱ ከፍተኛ ውኃ የሚፈልጉ እንደ ሩዝ እና ሱፍ የመሳሰሉ ሰብሎችን በበረሃማ አካባቢዎች በመስኖ ማምረቷ የውኃውን ሀብት ሆን ብላ የማባከን ዋነኛ ማሳያ ነው።
ሀገሪቷ በፈረንጆቹ 1929 እና 1959 በተደረጉ ኢፍትሃዊ የቅኝ ግዛት ውሎች አማካኝነት አሁንም የዓባይን ውኃ በብቸኝነት ለመቆጣጠር እና ሌላው ተፋሰስ ሀገር እንዳይጠቀም የመሻር መብት አለኝ ብላ ታምናለች።
ግብፅ ያለአግባብ በረሃ ላይ የምታባክነውን የውኃ ሃብት ማስተካከል ሲገባት፣ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለመገደብ የምታደርገው ሙከራ ጊዜ ያለፈበት የሴራ ፖለቲካ ነው።