አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ክብ ጠረጴዛ የበላይና የበታች፤ የራስጌና የግርጌ ልዩነት የሌለው በዙሪያው የሚቀመጡ ሰዎችን ሁሉ በእኩልነት በክብር የሚያስተናግድ ታላቅ የማህበራዊና የፖለቲካ እሴት መገለጫ ነው።
ክብ ሰርቶ በመቀመጥ የመምከር ልምምድ በኢትዮጵያውያን ባህላዊ የውይይትና የእርቅ ስነ ስርዓቶች ውስጥ ለዘመናት የዘለቀ እሴት መገለጫ ነው፡፡
በጠረጴዛ ዙሪያ የመቀመጥ መርህ ሁሉም ተሳታፊዎች ሀሳብ በመግለጽ እንዲሁም በውሳኔ ሰጪነት እኩል የመሳተፍ ነጻነትና መብት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚከተለውን የአሳታፊነት መርህ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
ኮሚሽኑ በተለያዩ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የማህበራዊ አስተሳሰብ ልዩነቶች መካከል ያሉ ቅራኔዎችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ልክ እንደ ክብ ጠረጴዛ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በእኩል የውይይት መድረክ ላይ እያሳተፈ ይገኛል፡፡
ይህ አካታች አሰራር ማንኛውም ወገን ከሌላው ሳይበልጥ፤ ደግሞም ሳይተናነስ፤ የሀገሪቱን የቆዩና ስር የሰደዱ ችግሮች በነጻነትና በግልጽነት እንዲወያይባቸው ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
አንዱ የሌላውን ድምጽ ሳይደፈጥጥ፤ ሁሉንም በእኩል የባለቤትነት ስሜት የሚያሳትፍ የምክክር መድረክ መኖሩ የጋራ መግባባትን ለመፍጠርና ለዘላቂ ሰላም መሰረት ለመጣል ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ይህ በክብ ጠረጴዛ እኩልነት የተቃኘው የኮሚሽኑ ጉዞ በተግባር ሲተረጎም የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች በውይይትና በጋራ ስምምነት ለመፍታት የሚያስችል ትልቅ ተስፋን ይዞ ብቅ ብሏል።
ኮሚሽኑ ላለፉት አራት ዓመታት ከ1ሺህ 200 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ውስጥ የአጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሁም የአጀንዳ እና የተሳታፊ ልየታ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በዚህ ሂደት በሕዝቡ የተወከሉ 4 ሺህ ተሳታፊዎችን በመያዝ ከሦስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአሁኑ ወቅት እጅግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
በጉባኤው ላይ ስምንት ዋና ዋና ስልታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የሁሉንም ሀሳብ በእኩልነት የሚያስተናግድ ጥልቅ ምክክር እየተደረገ ነው፡፡
የምክክሩ ተሳታፊዎች የሀገርን የጋራ ጥቅም በማስቀደም ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት በሚጥሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ጠረጴዛ ዙሪያ ወደመግባባት እየመጡ ይገኛል፡፡
በእመቤት ሲሳይ