አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 477 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል አለ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው ÷ ከተለያዩ የኃይል ምንጮች የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት መጠን ለማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል፡፡
በዚህ መሰረትም በ2018 በጀት ዓመት ከተለያዩ የኃይል ምንጮች ከ9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻሉን አመልክቷል፡፡
በተገኘው የኤሌክትሪክ ኃይልም በከተማና ገጠር አካባቢዎች ያለውን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ይበልጥ በማጠናከር በርካታ ዜጎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቅሷል፡፡
በዚህም በዓመቱ ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 427 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 477 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ሚኒስቴሩ አረጋግጧል፡፡
የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ሽያጭ መጠንን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ሲሆን ÷ በ2018 በጀት ዓመት 31 ሺህ 583 ጊጋ ዋት ሰዓት ለመሸጥ ታቅዶ ከ34 ሺህ 25 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ መሸጡ ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣይ በቀጣናው ያላትን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረትና በቅንጅት እንደምትሰራ ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገደፍ