የሀገር ውስጥ ዜና

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በፋግታ ለኮማ ወረዳ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራን አስጀመሩ

By Melaku Gedif

August 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ፋግታ ለኮማ ወረዳ ነቸላ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል፡፡

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ የአኗኗር ዘይቤ በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

ፕሮግራሙ በከተማና ገጠር መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትስስር ከማሳለጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት መቀየር እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡

በፋግታ ለኮማ ወረዳ ነቸላ ቀበሌ የተጀመረውን የገጠር ኮሪደር ሥራ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚያከናውነው ተናግረዋል፡፡

የመደመር መንግሥት እሳቤ የሆነው በጎ ፈቃድ አገልግሎት መተሳሰብ እና መረዳዳትን ከማጎልበት ባለፈ የሕሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በገጠር ኮሪደር የሚሰሩ ሞዴል መንደሮች በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ መሆናቸው መርሐ ግብሩን ይበልጥ ለማጠናከር እድል እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የነቸላ ቀበሌ የገጠር ኮሪደርን በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጻቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ባለሙያ በላይነሽ አበበ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በገጠር ኮሪደር ልማት ሥራው ለሌሎች አካባቢዎች ተምሳሌት የሚሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡ አረጋግጠዋል፡፡

ዜጎች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በንቃት በመሳተፍ እርዳታ ለሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ