የሀገር ውስጥ ዜና

የባሕር ዳር ከተማን ገቢ ለማሳደግ ሰላምን ማጽናት አስፈላጊ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By abel neway

August 06, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር ዳር ከተማን ገቢ ለማሳደግ ሰላምን ማጽናት አስፈላጊ ነው አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱን ተርሚናል መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በባሕር ዳር ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋን የሀብት እንቅስቃሴ ማዕከል የሚያደርግና ውበቷን ይበልጥ የሚገልጥ ነው፡፡

ከተማዋ ታሪክና ተፈጥሮ ሳይሰስቱ ውበት ያበዙላትና ለኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለአፍሪካውያን የልማት፣ የብልጽግናና የእድገት ምሳሌ መሆን የምትችል ናት ብለዋል፡፡

ባሕር ዳር ከ100 ዓመታት በፊት ከመሀል ሀገር ከሸዋ፣ ከወለጋ ወደ ጎንደር በሚደረገው ጉዞ እና የንግድ እንቅስቃሴ ድልድይ ሆና ለረጅም ጊዜ ያገለገለች ከተማ መሆኗን አውስተዋል፡፡

ለዚህም በጎርጎራና በባህርዳር መካከል ለነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በጊዮርጊስ ግቢ ከ200 አመታት በፊት የተገነባው ማረፊያ ግንብ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በዚያ መጠን ንግድ ተስፋፍቶ ልማት ሊያመጣ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ባለመሰራቱ ባሕር ዳርን ማየት በሚገባን ልክ ሳናይ ቆይተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ ታሪክን መለስ ብሎ በማየት መልካም ጅማሮ መኖሩን አንስተዋል፡፡

በቅርቡ የጎርጎራ ሪዞርትን እንዲሁም በባሕር ዳር ፈለገ ጊዮንን በመገንባትና ሁለቱን ለማገናኘት በኢትዮጵያ ትልቋን መርከብ ጣና ነሽ ጨምሮ በርካታ መርከቦችን በማምጣት ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገባውን ውጤት ለማግኘት ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ቀዳሚ የሆነው የውስጥ ለውስጥ መንገድ በጥሩ ዲዛይን ከተሰራባቸው ከተሞች ከፍተኛውን ስፍራ የምትይዘው ባሕር ዳር መሆኗን ጠቅሰው፥ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በቀጣናው በጥራቱና በግዝፈቱ ሊተካከለው የማይቻል ድልድይም በዚሁ ከተማ ተገንብቷል ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ስራም ከተማዋን የሀብት እንቅስቃሴ ማዕከል መሆን የሚያስችላትና ውበቷን ይበልጥ የሚገልጥ ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ የሚገኘው ስታዲየም ሲጠናቀቅ የሀገር ውስጥና አህጉራዊ ውድድሮችን ጭምር የሚያስተናግድ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በተሰራው ሪፎርም የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ከቢሯቸው ሆነው በቨርቹዋል አጠቃላይ የፍትህ ስርዓቱን መከታተል የሚያስችል አስደናቂ ስራ ተሰርቶ በማየቴ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለው ነው ያሉት፡፡

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ የተገነባው የባህር ዳር ከተማ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል የተጠቀሱትን የልማት ስራዎች ለማከናወን ትልቅ ብስራት ነው ብለዋል፡፡

እንደዚህ ያለውን እድገት ለማስቀጠል ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች የግድ ሊሟሉ እንደሚገባ ጠቁመው፥ በገነባን ቁጥር በርከት ያሉ ሰዎች እያመጣን የከተማዋን ገቢ ማሳደግ አለብን ነው ያሉት፡፡

ከተማዋ በገቢ ከኢትዮጵያ ከተሞች 7ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ ለቱሪስት ምቹ ከባቢን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ሰላም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት ሰላምን ማረጋገጥ ካልተቻለ ያየናቸው የእድገት ተስፋዎች ሊበላሹ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ጊዜ እና ዘመን ሳያልፍ የተገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ በመግለጽ፥ በትብብርና በጋራ በመቆም ውድ ስጦታ የሆነውን ሰላም ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው የፖለቲካ ልዩነቶችና ፍላጎቶችን በውይይትና በድርድር ብቻ የመፍታት ልማድ ሊዳብር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በአቤል ነዋይ