አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው አሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፡፡
ፓርቲው የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደትና የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አፈጻጸምን አስመልክቶ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች ገለጻ አድርጓል፡፡
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ከለውጡ ወዲህ የተመዘገቡ ድሎች “የመደመር” ፍልስፍናን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ዓለም ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በስደት የነበሩ ፖለቲከኞች ወደ ሀገር መመለስና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የተፈጠረው የትብብር መንፈስ ለሀገራዊ አንድነት ትልቅ ሚና እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ 15 ነጥብ 9 ሚሊየን አባላት እንዳሉት ገልጸው፥ በዚህም ከአፍሪካ ቀዳሚ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ 11ኛው ትልቁ ፓርቲ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተመዝግበው ከ94 በመቶ በላይ ታሪካዊ የመራጮች ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ገልጸው፤ ምርጫው ለመላው ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡
በምርጫው ሂደት ዙሪያ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የተዛቡ ግንዛቤዎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ሕዝቡ በባለቤትነት በመቆም ምርጫውን በድል ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የከተሞች አስደናቂ ለውጥ በፓርቲውና በህዝቡ መካከል ያለውን ትስስር አጠናክሮታል ነው ያሉት።
የመደመር ፍልስፍና የአመራሩ፣ የህዝቡና የባለድርሻ አካላት የጋራ እሴት ሆኖ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሻገረ ነው ብለዋል፡፡
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተመዘገበው ውጤት ለገዢው ፓርቲ ህዝቡ የሰጠው አዲስ አደራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፓርቲው የገባውን ቃልኪዳን ወደ ተግባር እየቀየረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን፣ ብሔራዊ መግባባትንና ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በመካሄድ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የማይተካ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ የታደሙ ዲፕሎማቶች በበኩላቸው የኢትዮጵያን የዴሞክራሲና የምርጫ ስኬት አድንቀዋል።
በመሳፍንት ብርሌ