የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ አበባ – ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነትና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት

By tigist gizachew

August 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻና በመልሶ ማልማት ውብ፣ ጽዱና ማራኪ ከተማ ሆናለች፡፡

የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና መልሶ ማልማት የከተማዋን ገጽታ ቀይሮታል፡፡ መንገዶች ከነሙሉ መሠረተ ልማታቸው ሰፍተው ዘመናዊ ሆነዋል፡፡

ሰፊና ጥራት ያላቸው አስፋልት መንገዶች፣ ምቹ የሆኑ ንጹህ የእግረኛ መንገዶች እና የብስክሌት መንገድ፣ የመብራትና የውበት ሥራዎች እንዲሁም አረንጓዴ ማረፍያ ቦታዎች በብዛት ተሰርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞችና አካባቢያቸው ከብክለት ጸድተው የዕረፍትና መዝናኛ ቦታዎች ሆነዋል፡፡የመዲናዋ አረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ አድጎ ውብ ማራኪ ከተማ ሆናለች፡፡

አዲስ አበባ አሁን ላይ በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽትም የሚዝናኑበት ከተማ ሆናለች፡፡በከተማዋ የሚገኙ ሙዚዬሞች፣ ፓርኮች፣ ታሪካዊ ቅርሶችና የባህል ማዕከላት ውብ ሆነው ታደሰዋል፡፡

ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ ስብሰባዎች የሚስተናገዱባቸው የኮንፈረንስ ማዕከላትም ተገንብተዋል፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ለቱሪስቶች ረዘም ላሉ ቀናት እንዲቆዮ የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች አሏት፡፡

በዚህም የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የውጪ ቱሪስቶች ቁጥር ከነበረበት 123 ሺህ 489 ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አድጓል።

የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ከነበረበት 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ወደ 1ዐ ነጥብ5 ሚሊየን ማደጉን የከተማዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በተለየ ሁኔታ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ ተካሂደዋል፤ እየተካሄዱም ይገኛል፡፡ በእነዚህ ኮንፈረንሶች ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶች ከተማዋንና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ፡፡

ዓለም ዓቀፍ ጎብኝዎች አዲስ አበባ ላይ ረዘም ላሉ ቀናት ይቆያሉ፡፡ አዲስ አበባ ዛሬ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት እንዲሁም ተመራጭ የዓለም ዓቀፍ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች ትገኛለች፡፡