የሀገር ውስጥ ዜና

በወጣቶች ህይወት የሚቆምረው ህገ ወጡ ህወሓት

By Mikias Ayele

August 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የህገ ወጡ ህወሓት የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳና እና  የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ለትግራይ ክልል ወጣቶች ስደት፣ እስር፣ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡

ወጣት የማህበረሰብ ክፍል ለአንድ ሀገር መጻኢ ጊዜ ተስፋ፣ የፈጠራ እና የዕድገት ዋና ሞተር ነው፡፡ ይህ የማህበረሰብ ክፍል ችግር ሲገጥመው የሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ይወድቃል።

በአሁኑ ወቅት በጦርነት ጉሰማ እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት በሚታመሰው የትግራይ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች ለጥቂት ግለሰቦች ስልጣን ማሰንበቻ ሲባል በግዳጅ እየታፈሱ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንዲገቡ እየተደረጉ ነው። ይህን የግዳጅ አፈሳ በመፍራት ወጣቶች ለስደት፣ ለጭንቀትና ለእስር እየተዳረጉ ነው፡፡

ከጦርነቱ ማግስት በትግራይ ወጣቶችና ታዳጊዎች ዘንድ የስነ ልቦና ችግር  እና የአዕምሮ መቃወስ ተጋልጠዋል።

ለዚህ አሳሳቢ የወጣቶች የስነ ልቦና ችግር ዋነኞቹ ምክንያቶች የጦርነት ትውስታ፣ የኢኮኖሚ መውደቅ፣ የስራ አጥነት መስፋፋት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በክልሉ የተደቀነው የዳግም ጦርነት ስጋትና የጸጥታ እጦት ናቸው።

የትግራይ ወጣቶች የወደፊት ህይወታቸው እንዲመሰቃቀል እና ተስፋ እንዲቆርጡ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል በክልሉ እየተካሄደ ያለው የአስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ወይም የአፈሳ ዘመቻ ዋነኛው ነው።

ሂውማን ራይትስ ዎች እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዳረጋገጡት፤ የህገ ወጡ ህወሓት ታጣቂዎችና የአካባቢው ባለስልጣናት ወጣቶችንና ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ጭምር ከየመንገዱ፣ ከስራ ቦታዎች፣ ከዕምነት ተቋማት፣ ከወርቅ ማውጫዎች እና በቤት ለቤት አፈሳ በማካሄድ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች እየተጋዙ ይገኛሉ።

ይህንን ድርጊት ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ህገ ወጡ ህወሓት በቅርቡ ያዘጋጀው እና የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን ህጋዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስበት አፋኝ ረቂቅ አዋጅ ነው።

ይህ አዋጅ ወታደራዊ ምልመላን የሚቃወሙ፣ የሚተቹ ወይም ፍቃደኛ ያልሆኑ ወጣቶችን እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ከማስቀጣቱ በተጨማሪ በሞት ሊያስቀጡ የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን የያዙ ናቸው፡፡

አዋጁ ወጣቶችን በክልላቸው ብሎም በሀገራቸው በነጻነት የመኖር መብታቸውን የሚነፍግና በግዳጅ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡም እያደረጋቸው ነው።

ይህንን የግዳጅ ውትድርና እና ዳግም ለጦርነት የመማገድ ዕጣ ፈንታ ለመሸሽ በትግራይ የሚገኙ ወጣቶች ብቸኛ አማራጭ መሰደድና መሸሽ ሆኗል።

ወጣቶች አፈሳውን ለመሸሽ ሲሉ ከቤታቸው ጠፍተው በየዱሩና በየዘመዶቻቸው ቤት እንደሚደበቁ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ሪፖርቶች ያሳያሉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ደግሞ አደገኛውን የስደት መስመር በመምረጥ ወደ ጎረቤት ሀገራት እና በብዛት ወደ አዲስ አበባና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች እየተሰደዱ ይገኛሉ።

በዚህ አስከፊ ስደት ምክንያት በትግራይ የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች እንደ መቐለ፣ ዓድዋ፣ ሽረ፣ አክሱም ያሉት በከፍተኛ ሁኔታ ወጣት አልባ እና “ሰው አልባ” እየሆኑ መምጣታቸውን የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ትውልድና ሀገር የሚረከበውና የሚያስቀጥለው ወጣት ኃይል ክልሉን ጥሎ እየወጣ በመሆኑ፣ በትግራይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋል።

የወጣቱን ትውልድ የመማር፣ የመስራት፣ የመለወጥ እና ነገን ተስፋ የማድረግን መብት እየነጠቀ የሚገኘው ህገ ወጡ ህወሓት የትግራይ እናቶችን ማቆሚያ በሌለው ሐዘንና ስቃይ ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓል።

ካለ ጦርነት መኖር የማይችለው ህገ ወጡ ህወሓት፣ አሁንም ከውጭ ጠላቶችና ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን እና የቀጣናውን ሰላም እና ልማት ለማደፍረስ እየሰራ ነው፡፡

የዚህን የጸረ ሰላምና ጸረ ልማት ቡድን ድርጊት ለማክሸፍ መላው ኢትዮጵያዊያንና የክልሉ ህዝብ በአንድነት ሊቆሙና ሊቃወሙ ይገባል፡፡

በእመቤት ሲሳይ