አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሞ ሕዝብ ልዩነቶች ቢኖሩት እንኳን እንደቤተሰብ ይመክራል እንጅ ለፖለቲካ ሴራ መጋለጥ የለበትም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ሳይሳኩ የቆየባቸውን ሶስት ምክንያቶች አብራርተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም አንድ ክፍለ ዘመን በሚሻገረው የኦሮሞ ትግል ውስጥ ስትራቴጂካዊ ንድፈ ሃሳብ አለመኖሩ የመጀመሪያ ምክንያት መሆኑን እና ትግሉን እንዳዘገየው ተናግረዋል፡፡
ምርታማ ለመሆን የምርት ግብዓቶች አስፈላጊ ቢሆኑም ዘር ከሌለ ግን ማምረት እንደማይቻል ሁሉ፣ በኦሮሞ ትግል ውስጥ ጥያቄዎች ቢኖሩም ጥያቄዎች እንዲመለሱ ስትራቴጂ ነድፎ እና አቅምን አዘጋጅቶ መሄድ ላይ ችግር እንደነበር አውስተዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የነበሩ ልዩነቶች የኦሮሞ ትግል እንዲዘገይ ማድረጋቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በህዝቡ ዘንድ መረዳዳት እና ማንነቱን እና የትግሉን ጉዞ መረዳት ላይ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ በሰፊ ጂኦግራፊ መሬት ላይ የሚገኝ መሆኑ እንዲሁም የተለያዩ እምነቶች እና የፖለቲካ አመላካከቶች መኖራቸው የኦሮሞን ትግል ወደ ኋላ ሲጎትቱ ነበር ብለዋል፡፡
ትግሉ እዚህ ላይ ደርሶ እና አብዛኛው የኦሮሞ ጥያቄዎች ተመልሰው እንኳን መጥፎ አመለካከቶች እና የፖለቲካ ሴራዎች በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ መለያየትን እየፈጠሩ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
እንደ ኦሮሞ ስንፈልግ በወንዝ፣ ስንፈልግ በእምነት፣ ስንፈለግ በዞን መለያያችን ብዙ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ÷ አሮሞ አንድ ቤተሰብ ሆኖ ሳለ ትንንሽ ነገሮችን በውይይት መፍታት ስንችል ክፍፍል እንፈጥራለን ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ልዩነቶች ቢኖሩትም እንደቤተሰብ ይመክራል እንጅ ለፖለቲካ ሴራ መጋለጥ የለበትም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የጠላት መሳሪያ ሆነን አንድነታችን እየላላ ከሄደ የጠላት ፍላጎት እየተሳካ የኛ ድል ደግሞ እየራቀ ይሄዳል ነው ያሉት፡፡
ከተቃራኒ ሀይሎች ጋር ሩቅ መጓዝ የማይችል እና ከስትራቴጅካዊ የኦሮሞ ፍላጎት የራቀ ግንኙነት መፈጠሩ ሌላኛው የኦሮሞ ትግል ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጓደኛ ስትመርጥ ፀባዩን ባህሪውን ታያለህ እንጂ ዝም ብለህ አትመርጥም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከተቃራኒ ሀይሎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ስትራቴጂክ ካልሆነ የትግሉ ዓላማ ላይሳካ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
እነዚህ ችግሮች በኦሮሞ ትግል ውስጥ ሲታዩ የቆዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ