የሀገር ውስጥ ዜና

የኦሮሞ ሕዝብ በሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ በግልጽ ይታያል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

August 08, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኦሮሞ ሕዝብ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶና ላቡን አፍስሶ በሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ በግልጽ ይታያል አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ የኦሮሞ ሕዝብ በዘመናት ታሪኩ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ከስርዓቱ መበላሸት ውጪ በኢትዮጵያ ላይ ተቃውሞ አያውቅም፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ሁልጊዜም ቢሆን ከስርዓቱ እንጂ ከሀገሪቱ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በቦረና ሕዝብ ዘንድ ነፃነት ህግ ነው፤ ህግ ባለበት ቦታ ሁሉ ነፃነት እና ሰላም አለ የሚል እምነት መኖሩን በማውሳት፥ የኦሮሞ ሕዝብ ሀገር ለመገንባት ያበረከተው ትልቅ አስተዋፅኦ በግልጽ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ አጥንቱን ከስክሶ፤ ደሙን እና ላቡን አፍስሶ ይህችን ሀገር መገንባቱን ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ዓለምም የመዘገበው ታሪክ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኦሮሞ ኢትዮጵያ ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ከኢትዮጵያ አይገነጠልም፤ አባቶቻችን በደም የገነቡት ሀገር በቃል ሊፈርስ አይችልም ነው ያሉት፡፡

የፈለገ ሰው አልተመቸኝም፤ መገንጠል እችላለሁ ብሎ ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፤ ኦሮሞ ግን ራሱ ኢትዮጵያ ሆኖ ሳለ ለመገንጠል የሚያነሳው ጥያቄ ስህተት ነው ብለዋል፡፡

ኦሮሞው ሁሉንም ሕዝብ አቅፎ አሳድጎ የራሱ እንደሚያደርግ ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለትልቅ ሕዝብ የማይመጥን ዓላማ ይዞ መነሳት ግን ትክክል ያልሆነ ስም ያሰጣል ነው ያሉት፡፡

በቤተልሔም ግርማ