አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌደራል መንግስት የ2019 በጀትን 2 ነጥብ 34 ትሪሊየን ብር ማጽደቁ አይዘነጋም፡፡ ይህ ግዙፍ በጀት፣ ሀገሪቱ የጀመረችውን ሁለገብ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሽግግር ለማስቀጠል፣ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን እና የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው፡፡ ይህ በጀት ከቀደመው ዓመት የ1 ነጥብ 93 ትሪሊየን ብር በጀት ጋር ሲነጻጸር በ411 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወይም የ21 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ ያሳየ የሀገሪቱ ትልቁ በጀት ነው፡፡ በጀቱ የተቀረጸው በተግባር ላይ ከዋለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓላማዎች እና የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ጋር በተስማማ መልኩ ነው፡፡ የበጀቱ አወቃቀር የመንግሥትን መደበኛ ሥራዎች ከማስቀጠል ባለፈ ለክልሎችና ለካፒታል ፕሮጀክቶች ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ 1 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር ወደ 53 በመቶ ገደማ ለመንግሥት መደበኛ ሥራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን፣ ለልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ደግሞ 568 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ለክልል መንግሥታት የ520 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ጥቅል ድጋፍ እና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14 ቢሊዮን ብር ተለይቷል፡፡ በዚህም መንግሥት ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ የውጭ ዕርዳታ ጥግግትን በመቀነስ፣ 1 ነጥብ 49 ትሪሊየን ብር ከሀገር ውስጥ የታክስ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ የሀገር ውስጥ ገቢን አማጥጦ ለመሰብሰብ የተያዘው ውጥን በሀገሪቱ ማክሮ-ኢኮኖሚ፣ በግሉ ዘርፍ እና በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ሰፊ አዎንታዊ አንደምታዎች አሉት። በማክሮ-ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን አንደምታ ስንመለከት የበጀት ጉድለትን በራስ አቅም ለመሙላት፣ የውጭ ዕዳ ጫናን ለመቀነስና የፖሊሲ ሉዓላዊነትና የውሳኔ ሰጪነት ነፃነትን ለማረጋገጥ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም በግሉ ዘርፍ ላይ ፍትሃዊ የገበያ ውድድርን ለመፈጠር፣ በመሠረተ-ልማት መሻሻል ተጠቃሚ መሆን እንዲቻልና የዲጂታላይዜሽንና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠንም ያግዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል፣ ዘላቂ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር እና በዜግነት ኩራትና በሀገር ባለቤትነት ስሜት መዳበር ላይም የሚኖረው አንደምታ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ የታክስ አሰባሰብ ውጥን ስኬታማ እንዲሆንም መንግሥት አዲሱ የታክስ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያዎችን ተግብሯል፡፡ ለካፒታል ወጪ ከተመደበው ሰፊ በጀት ውስጥ ለኮሪደር ልማት፣ ለኃይልና ለትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ቅድሚያ የሰጠ ነው፡፡ ይህም የሀገር ውስጥ የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የመስታወትና የሴራሚክስ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በስፋት የሚያቀርቡበት ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥራል፡፡ መንግሥት ለነዳጅ እና ለማዳበሪያ ድጎማ ከሚያደርገው ከፍተኛ በጀት በተጨማሪ፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት የውጭ ምንዛሪ ጫናን የመቀነስ ስትራቴጂውን ያግዛል፡፡ የበጀት ድልድሉ ለክልሎች የልማት አቅም ማደግም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ለክልሎች የተመደበው ከግማሽ ትሪሊየን ብር በላይ ድጋፍ፣ በክልል ደረጃ የሚከናወኑ የማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርና እና የኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል ፈጠራን በእጅጉ ያግዛል፡፡ የ2 ነጥብ 34 ትሪሊየን ብር ግዙፍ በጀት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ሰፋፊ አንደምታዎች ይኖሩታል፡፡ በጀቱ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀመጠውን እና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዓለም ፈጣን ከሚባሉት ተርታ የሚያሰልፈውን የ10 ነጥብ 2 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ለመምራት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ የተያዘው የ10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገትም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀዳሚዋ ሀገር ያደርጋታል፡፡