የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገራዊ ራዕይን የሚያሰናክለው ሌብነት

By Yonas Getnet

August 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ እድገት ጉዞ ውስጥ ሙስናና ሌብነት የተደመሩ አቅሞችን የሚያባክኑ፣ ክፍተቶችን የሚያሰፉና ሀገራዊ ራዕይን የሚያሰናክሉ አጥፊ ተግባሮች ናቸው፡፡

መልካም አስተዳደር በሕዝብና በመንግሥት መካከል በሚሰፍን እምነት የሚወሰን ሲሆን÷ ሙስናና ሌብነት ግን ይህንን የሕዝብ እምነት ያጠፋል።

ዜጎች በአገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ ብልሹ አሰራሮች ተንሰራፍተዋል ብለው ሲያስቡ፣ በመንግሥት ተቋማትና በሕግ የበላይነት ላይ ያላቸው እምነት ይሸረሽራል።

በብልሹ አሰራሮች ሳቢያ የሀገር ሃብት ሳይደክሙና ሳይለፉ በጥቂት ሕገ ወጥ ግለሰቦችና ስልጣንን ለግል ጥቅም በሚያውሉ አካላት እጅ እንዲከማች ይሆናል።

ይህም የዜጎችን ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳል፤ ማሕበራዊ ፍትሕን ያዛባል፤ በዜጎች መካከል የቁጣና የቅሬታ ስሜት ይፈጥራል።

የመደመር መንግሥት ሙስናን በዘመቻ ወይም በጊዜያዊ የእሳት ማጥፋት ሥራ ብቻ መከላከል እንደማይቻል በመገንዘብ፣ ችግሩን ከስሩ ነቅሎ መጣል የሚያስችሉ በርካታ መዋቅራዊ፣ ሕጋዊና ቴክኖሎጂያዊ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡

በማስረጃና በጥናት ላይ ተመስርቶ ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ ባለሃብቶችንና ደላሎችን ለህግ የማቅረብ ሥራዎችን አከናውኗል፤ እያከናወነም ይገኛል።

የተገልጋዮችንና የአገልግሎት ሰጪዎች ቀጥተኛ ንክኪ ለሙስና ዋናው በር በመሆኑ፣ መንግሥት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እና 2030 ስትራቴጂን በመተግበር በርካታ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ስርዓት እንዲቀየሩ አድርጓል፡፡

ለአብነት ያክል እንደ የንግድ ፈቃድ ማውጣትና ማደስ፣ የግብር፣ የወደብና የጉምሩክ አሰራሮች፣ የፓስፖርት አገልግሎቶችና የቪዛ አሰጣጥ ክፍያዎችን በዲጂታል ሥርአት እንዲከናወኑ በማድረግ ግልጽነትን ከመጨመሩም በላይ ለብልሹ አሰራር የመጋለጥ እድልን አጥቧል።

የባንክ አሰራርን ዘመናዊ በማድረግ፣ የቴሌብር፣ የሲቢኢ ብርና የሌሎች ዲጂታል ክፍያ አማራጮችን በማስፋፋት የጥቁር ገበያ፣ የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውርና የጉቦ ክፍያዎችን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም በመፍጠር ላይ ይገኛል።

የመሬት ይዞታዎችን በዲጂታል የካዳስተር ሥርዓት በመመዝገብ፣ በመሬት አስተዳደር ሥራዎች በሰፊው ይስተዋሉ የነበሩ ሕገ ወጥ አሰራሮችንና ደላላ ተኮር ሌብነቶችን ለመቀነስ ያስቻለ ርምጃ ተወስዷል።

በትምህርት ስርዓቱ፣ በተቋማትና በሕዝባዊ ሁነቶች የታማኝነት፣ የሀገር ፍቅር፣ የሰራተኝነትና የዜግነት ሀላፊነት እሴቶች እንዲጎለብቱ የማስተማር ሥራዎች በማካሄድ ሙስናንና በሕገ ወጥ መንገድ ሀብታም መሆንን የሚያወግዝ፣ በጥረቱና በስራው የሚበለፅግን ዜጋ የሚያከብር ማህበራዊ እሴት የመገንባት ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።

ሙስና ለረጅም ዘመናት ስር ሰዶ በመቆየቱ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሕብረተሰቡና ከተቋማት አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ማጽዳት ፈታኝ ቢሆንም የመደመር መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፋፊ ጥረቶችን በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችሏል።

ሙስናና ሌብነትን ማስወገድ የመንግሥት ብቸኛ የቤት ሥራ አይደለም፤ ይልቁንም የመላው ሕዝብ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የትምህርት ተቋማት የጋራ ሃላፊነት ነው።

እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ ሀብትና የሕግ የበላይነት ዘበኛ በመሆን፣ ሌብነትን በመጸየፍና በመታገል ለነገዋ ብልጽግናዋ የተረጋገጠች ኢትዮጵያ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል።

በመልካም ፈቃዱ