የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አዲስ አቅጣጫ

By Hailemaryam Tegegn

August 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት መሪነት ብሔራዊ ጥቅሟን፣ የሰላም ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ትስስርና የልማት ግቦቿን ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ ዲፕሎማሲዋን በሰፊው እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡

ዲፕሎማሲ አንዲት ሀገር ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በሰላማዊ መንገድ የምታስተዳድርበትና የጋራ ጥቅሞችን የምታሳካበት ዋነኛ መሳሪያ ነው።

ከግጭት ይልቅ ውይይትን፤ ከመገለል ይልቅ ትብብርን በማስቀደም ሀገራት የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ይገለገሉበታል።

በዘመናዊው ዓለም ዲፕሎማሲ ከፖለቲካዊ ግንኙነት ባለፈ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንትንና ንግድን ለማስፋት፣ በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች በትብብር ለመስራት እንዲሁም የሀገርን ገጽታ ለመገንባትና ተፅዕኖን ለማላቅ የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡

በመሆኑም ዲፕሎማሲ የውጭ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የሀገር ልማትና የብሔራዊ ጥቅም ማስፈጸሚያ አቅምም ነው።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመደመር መንግሥት መሪን ዲፕሎማሲን ለብሔራዊ ጥቅሞቿ መከበር፣ ለሰላም ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ ትስስርና የልማት ግቦችን ለማሳካት በሰፊው እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡

ለአብነትም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሰላምና የትብብር ግንኙነትን በማጠናከር ከጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር በንግድ፣ በመሰረተ ልማትና በቀጣናዊ ሰላም ዙሪያ ያከናወነቻቸው ሰፋፊ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከአፍሪካ፣ ከእስያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስሮችን ማስፋት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ዋና አቅጣጫ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን ጨምሮ የውሃ ሀብቷን በፍትሃዊና በምክንያታዊ መርህ የመጠቀም ህጋዊ መብቷን ለማስጠበቅ የዲፕሎማሲ አቅሟን አጠናክራ ቀጥላለች።

በተጨማሪም እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ የአረንጓዴ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ተነሳሽነቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላትን የትብብር ቁርጠኝነት አመላካች ናቸው፡፡

በአፍሪካ ኅብረትና በሌሎች የባለብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ተሳትፎ ማጠናከሯም ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን ይበልጥ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በአመለወርቅ ደምሰው