ዓለምአቀፋዊ ዜና

 የቀይ ባሕር ደህንነት ስጋት የሆነው የሁቲ አማጺያን ጥቃት

By Mikias Ayele

August 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሁቲ አማፂያን በጅቡቲ፣ ኤርትራ እና የመን አዋሳኝ በሚገኘው የባብ ኢል መንደብ መስመር በሚፈፅሙት ተደጋጋሚ ጥቃት የቀይ ባሕር ደህንነት ስጋት ውስጥ ወድቋል፡፡

አማፂያኑ በዛሬው ዕለት በትንሽ የጭነት መርከብ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ሶስት መርከበኞች መገደላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ጥቃቱ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ከተከሰተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በባብ ኢል መንደብ የንግድ መስመር በአማፂያኑ የተፈፀመ ጥቃት መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

ከኦማኗ ሰለላ ወደብ ተነስታ በጅቡቲ በኩል ወደ የመን እንቅስቃሴ ስታደርግ በነበረቸው ጀልባ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ሁለት የፓኪስታን እና አንድ የኢንዶኖዥያ ዜጋ ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል፡፡

ቡድኑ ቀደም ሲል ከፍተኛ አመራሮቹን በቀድሞ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኾሚኒ የቀብር ሥርዓት እንዲገኙ ለማድረግ ከቴህራን የተላከው አውሮፕላን ሳዔዲ በአየር ክልሏ እንዳያልፍ መከልከሏን ተከትሎ ከሪያድ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ ቆይቷል፡፡

ሳዑዲ ለፈፀመችው የአየር ክልል ክልከላ አፀፋም ቡድኑ የሳዑዲ ዓረቢያ የባሕር ሀይል በቀይ ባሕር እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ገደብ መጣሉን አስታውቋል፡፡

ከቀናት ግጭት በሁዋላ ቡድኑ በሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት የፈፀመ ሲሆን÷ የሳዑዲ አየር ሃይልም በቡድኑ ይዞታዎች ላይ የአፀፋ ጥቃት መፈፀሙ ይታወሳል፡፡

በሁቲ አማፂያን እና በሳዑዲ ዓረቢያ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በቀይ ባሕር የሚያልፉ መርከቦች ከፍተኛ የደሀንነት ስጋት ገጥሟቸዋል ነው የተባለው፡፡

አለም አቀፉ የንግድ ደህንነት ተቋም ኬፕለርን ጠቅሶ ሬውተርስ እንደዘገበው፣ቡድኑ ገደብ ከመጣሉ በፊት በባብ ኢል መንደብ የንግድ መስመር በቀን 50 መርከቦች ያልፉ የነበረ ሲሆን÷ ከክልከላው በኋላ ግን ወደ 32 ዝቅ ማለቱን አመላክቷል፡፡

በሚኪያስ አየለ