የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገር ፍቅር ጥልቅ ቁርኝት ማሳያ

By Melaku Gedif

August 11, 2026

ኢትዮጵያ ከተራራዎቿ የገዘፈ ታሪክ፣ ከወንዞቿ የጠለቀ ባህል እና ከልጆቿ አንድነት የተሰራች ታላቅ ሀገር ናት።

ሀገሪቱን በታሪክ አውድማ ላይ በኩራት እንድትቆም ካደረጓት አንዱ የሕዝቦቿ የማይበገር አርበኝነት ነው፡፡

ከዚያም በላይ ደግሞ ሕዝቦቿ ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ጥልቅ መንፈሳዊና አካላዊ ቁርኝት የተለየ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ከዚህ ጋር የተሰናሰለ ንግግር አድርገው ነበር፡፡

ይህም “እኛ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” የሚል ወርቃማ ንግግር ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተግባር እየኖሩት ያለ እና ጥልቅ የዘላለም ማንነት እና የሀገር ፍቅር ጽናት ማሳያ ነው፡፡

ይህ ጽንሰ ሀሳብ በደም የተጻፈና በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ የማይደበዝዝ የኢትዮጵያውያንን ዘላለማዊ ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ እውነታ ነው።

ይህ ቃል የፖለቲካ መፈክር ሳይሆን፣ የኢትዮጵያዊነትን ጥልቅ ፍልስፍና እና ለሀገር የሚከፈልን ዋጋ በአጭር ቃል የገለጸ ሕያው ምስክርነት ነው።

በእውነትም ሀገር የሌለው ሕዝብ ማንነት የሌለው፣ ተስፋውና ክብሩ የተገፈፈ ስደተኛ ነው። እኛ ግን ተከብረን የምንጠራው በእሷ ስም ነው፡፡

የትም ዓለም ብንሄድ፣ በኩራት ቀና ብለን እኔ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ስንል ክብራችንን የምንገልጽበት፣ የማንነት መታወቂያችን እሷ ናት፡፡

ስንኖር በለምለም ምድሯ ላይ ጥረንና ግረን ሀገራችንን እናለማታለን፡፡ ጠላት ክብሯን ሲነካ አፈሯን ከእግሩ አራግፈን ወደመጣበት እንሰድዳለን፡፡

ኢትዮጵያዊነት የሁላችንም ኢትዮጵያውያን መገለጫ ነው፡፡ ሕይወታችን፣ ስማችን፣ ክብራችንና ጥቅማችን ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር የተቆራኘ ነው። እሷ ስትኖር እኛ እንኖራለን፤ እሷ ስትከበር እኛ እንከበራለን።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን”፡፡