አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን የሚገነቡ እና ወደፊት የሚያራምዱ ጠንካራ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ነው አሉ ተመካካሪዎች ።
የ6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ በምክክሩ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዱ እና የቆዩ ችግሮቻችንን ሊፈቱ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።
ምክክሩ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ እና እንደ ሀገር የሚያስማሙንን ጉዳዮች የጋራ እያደረግን ለመቀጠል ትልቅ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሂደቱ ተሳታፊ መሆናቸው ሀገራዊ የፖለቲካ ባህላችን ምክክርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ገልጸዋል።
የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር እንዲሁም ተመካካሪው አልአዛር ዓባይነህ በበኩላቸው÷ ለዘመናት በዘለቁ አለመግባባቶች ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ስትፈተን መቆየቷን አስታውሰው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከምክክር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ገልጸዋል።
የምክክር ጉባዔው በሀገራዊ መግባባት የጸናች ኢትዮጵያን ለመገንባትና ለመጪው ትውልድ ብሩህ መሠረት ለመጣል ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በምክክሩ ለሀገር የሚጠቅም ሐሳብ በማበርከት የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ አካል በመሆናቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ነው ያወሱት፡፡
ይህ ወቅት በሀገሬ ያለኝ ተስፋ እጅግ የለመለመበት ወቅት ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ እና የሕግ ባለሙያ ወንድሙ ግዛው ናቸው።
ፍትሕ እና እኩልነት የሰፈነባትን የተሻለች ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ተመካካሪ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን መመልከታቸውንም አንስተዋል።