አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት ለመከላከል የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጉልህ ሚና አለው አሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፡፡
በድሬዋዳ “ጽዱ ኢትዮጵያን፣ ጽዱ ድሬዳዋን ለትውልድ” በሚል መሪ ሐሳብ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
ከንቲባ ከድር ጁሃር በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተጀመረው ንቅናቄ አካባቢዎች ከፕላስቲክ እና ከተረፈ ምርቶች እንዲጸዱ ተደርጓል፡፡
በዚህም የውሃ መገኛ ስፍራዎችና ሌሎች ቦታዎች ጽዱ መሆን መጀመራቸውን ገልጸው÷ የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር የወጡ ሕግና ደንቦችን ተፈጻሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በበኩላቸው÷ ባለፉት ሁለት ዙሮች በተከናወነው ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ጤናማና ጽዱ አካባቢዎችን መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተለይም አካባቢን ከፕላስቲክ ምርቶች ጽዱ ለማድረግ በተሠራው ሥራ እንዲሁም የፕላስቲክ አያያዝ ላይ የወጣው አዋጅ ተግባራዊ መደረጉ አካባቢዎች ከፕላስቲክ ምርቶች እንዲጸዱ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአስተዳደሩ በተተገበሩ ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄዎች የፕላስቲክ፣ ድምፅ እና ሌሎች ብክለቶችን መከላከልና መቆጣጠር መቻሉ ተመልክቷል፡፡
በመቅደስ ደረጀ