አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ የነፃነትና የአፍሪካውያን የአንድነት ተምሳሌት ብትሆንም፣ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የገጠሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች በዲፕሎማሲው መስክ የሌሎችን አጀንዳዎች እንድትቀበልና በጥገኝነት ስሜት ውስጥ እንድትቆይ አድርገዋት ቆይቷል።
ይሁን እንጂ በቅርብ ዓመታት የተቀረጸውና በመደመር ፍልስፍና የሚመራው አዲሱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀገሪቱን ከዚህ አጀንዳ ተቀባይነትና ጥገኝነት በማላቀቅ፣ ታሪኳን፣ ታላቅነቷንና አሁን ላይ እያደገች የመጣችበትን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፍጥነት የሚመጥን ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን አጎናፅፏታል።
ይህ አዲስ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ የራሷን ዕድል በራሷ እንድትወስንና ብሔራዊ ጥቅሟን በጽኑ መሠረት ላይ እንድታስከብር እያደረጋት ይገኛል።
አዲሱ የዲፕሎማሲ ማዕቀፍ ሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ራስን የመቻል መንገድ እንድትቀይስ ያስቻሉ በአራት ዓበይት ምሰሶዎች ላይ የተቃኘና የሚመራ ነው፡፡ እነዚህ ምሰሶዎችም ንቁ ተሳታፊነት፣ አማራጭ ዲፕሎማሲ፣ ተላማጅነትና ገቢር ነበብነት እንዲሁም አጀንዳ ቀራጭነት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ መድረኮች ላይ ታዛቢ ከመሆን ወጥታ፣ በንቃት ድምፅ የምታሰማና ውሳኔዎችን የምታስተናግድ ንቁ ተሳታፊ ሆናለች። በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነትን ከመጠበቅ ጀምሮ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ያላት ተሳትፎ የዚሁ መርህ ማሳያ ነው።
ዲፕሎማሲን ከአንድ ወገን ወይም ከአንድ የፖለቲካ ጎራ ፍላጎት ጋር ብቻ ከማሰር በመውጣት፣ ሀገሪቱ የሁሉንም ወገን ጥቅም መሠረት ያደረገ ሁለንተናዊና አማራጭ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ትከተላለች። ይህ አካሄድ በምስራቅም ሆነ በምዕራብ ካሉ የተለያዩ የኃይል ሚዛኖች ጋር ያላትን ወዳጅነት እንድታጠናክርና አማራጮቿን እንድታሰፋ አድርጓታል።
በየጊዜውና በፍጥነት የሚለዋወጠውን የዓለም ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ በጥበብ በመከታተል፣ ሀገሪቱ ከሁኔታዎች ጋር ራሷን የምታላምድበትና ጥቅሟን ሳታስደፍር፣ ተላማጅና ገቢር ነበብ ተለዋዋጭ ስልቶችን የምትቀይስበት ብቃት ገንብታለች።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የሌሎችን ፍላጎትና አጀንዳ ዝም ብላ ከመቀበል ይልቅ፣ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና ለአካባቢውም ጭምር ጠቃሚ የሆኑ አጀንዳዎችን ቀርፃ የምታቀርብና በዓለም መድረክ ላይ ተፅዕኖ የምትፈጥር ሀገር ሆናለች።
የመደመር መንግሥት ተግባራዊ ያደረጋቸው የዲፕሎማሲ ሥራዎች የእነዚህ አራት መርሆዎች ሕያው ማሳያ ናቸው። ሀገሪቱ ያጋጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ በመቋቋም ብሔራዊ አንድነቷንና ጥቅሟን ማስከበር ችላለች።
ለአብነት ያህል፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን መቻሏ የአማራጭና የአጀንዳ ቀራጭ ዲፕሎማሲዋ ትልቁ ማሳያ ነው። ይህ ስኬት ሀገሪቱ በአዲሱ የዓለም የኃይል ሚዛን አሰላለፍ ውስጥ ያላትን ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ያረጋገጠ ነው።
በተጨማሪም በአፍሪካ ቀንድና በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተከተለችው የብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር እና የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን የመፍታት መርህ፣ የአጀንዳ ቀራጭነት ሚናዋን በጉልህ አሳይቷል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተደረጉ ድርድሮችና የተመዘገቡት ስኬቶች ሀገሪቱ የሌሎችን ጫና ውድቅ በማድረግ ብሔራዊ ጥቅሟን በራሷ አጀንዳ እንዴት ማስከበር እንደምትችል ያሳየችበት ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነው።
እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች አየር ንብረት ለውጥንና የአረንጓዴ አሻራ ልማትን በተመለከተ ያቀረበቻቸው ሀሳቦች በአህጉር ደረጃ ተቀባይነትን አግኝተው አጀንዳ መሆን ችለዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን የአዲስ ዲፕሎማሲ ቁመናዋን በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችሏትን የውስጥ አቅሞች በጽኑ መሠረት ላይ በፍጥነት እየገነባች ትገኛለች። የትኛውም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያለ ጠንካራ የውስጥ አቅም ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል በመረዳት፣ በመደመር መንግሥት በኩል ሦስት ዓበይት ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡
አንደኛው የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን መተግበርና የቱሪዝም እንዲሁም የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ማነቃቃት የዲፕሎማሲው ዋነኛ ደጋፊ ሆኗል።
ሌላኛው የመከላከያ አቅምን ማሳደግ ነው፡፡ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅና በአካባቢው አስተማማኝ የሰላም ዋስትና ሆኖ ለመቀጠል ዘመናዊና የተደራጀ የመከላከያ አቅም እየተገነባ ይገኛል።
ሦስተኛው የሕዝብ ለሕዝብና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ነው፡፡ ከጎረቤት ሀገራትና ከዓለም ማኅበረሰብ ጋር ያለውን ወዳጅነት በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም ዲጂታል ዲፕሎማሲንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በስፋት መጠቀም ሀገሪቱ በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ እንድትጓዝ እያገዛት ነው።
የኢትዮጵያ የመደመር መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀገሪቱ በታሪኳ ካላት ታላቅነትና አሁን ላይ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመ ስትራቴጂካዊ ምዕራፍ ከፍቷል። ንቁ፣ አማራጭ፣ ተላማጅና አጀንዳ ቀራጭ የሆኑት አራቱ ዓበይት መርሆዎች ሀገሪቱ በጥገኝነትና በአጀንዳ ተቀባይነት እንድትደቆስ የሚፈልጉ ውጫዊ ጫናዎችን በብልሃት እንድትመክት አስችለዋታል።
የመደመር መንግሥት ያስመዘገባቸው የዲፕሎማሲ ስኬቶች ይህንን እውነታ በተግባር ያረጋገጡ ናቸው። ይህንን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ዘላቂ ለማድረግ እየተገነባ ያለው የኢኮኖሚ፣ የመከላከያና የቴክኖሎጂ አቅም ደግሞ ሀገሪቱ ወደፊት ለምትጓዝበት የብልጽግና ስምሪት አስተማማኝ ከላላ ሆኖ ያገለግላል።
ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችውን ስትራቴጂካዊ ራስን የመቻልና የዲፕሎማሲ ልዕልና ጉዞ አጠናክራ በመቀጠል በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ መድረኮች ያላትን ስፍራ ይበልጥ ታሳድጋለች።