አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተሳታፊ ግለሰቦችና ቡድኖች እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎችን እየመረመርን ውሳኔ እንሰጣለን አሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ፡፡
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን አሁናዊ ሁኔታ አስመልክተው በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከተመካካሪ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እየተቀበለ መሆኑን ገልጸው፥ በምክክሩ የቅሬታ አፈታት ስነ ስርዓት መሰረት ጉዳዩ እየተጠና ውሳኔ እየሰጠን እንሄዳለን ብለዋል፡፡
የምክክር ሂደቱ በእቅዳችን መሰረት እየተከናወነ ነው ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፥ አሁን ላይ ሦስት አራተኛ ያህሉ ሥራ መገባደዱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ አለመግባባቶች አልነበሩም ማለት እንደማይቻል አንስተው፥ እነዚህ አለመግባባቶችና ግጭቶች ምክክሩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ የተረዳንበት ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም ተመካካሪዎቹ እነዚህን አለመግባባቶችና ግጭቶች በመደማመጥ መፍታት መቻላቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም እያንዳንዳቸው 500 ተሳታፊዎች ያሏቸው ቡድኖች ሲመካከሩ ቆይተው አብዛኞቹ መግባባት ላይ የደረሱባቸውን ምክረ ሃሳቦች አጽድቀው ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይ በተመካካሪዎች የፀደቁ የመጨረሻ ምክረ ሃሳቦችን እንደሚያሳውቅ ተመላክቷል፡፡
በእመቤት ሲሳይ