የሀገር ውስጥ ዜና

ሕገ ወጡ ህወሓት የሚፈጽመውን አፈሳና ግድያ ለማስቆም ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች በቁርጠኝነት ሊታገሉ ይገባል- የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ

By amele Demisew

August 13, 2026

 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ ህወሓት በወጣቶች ላይ እየፈጸመ ያለውን አፈሳ እና ግድያ ለማስቆም ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች በቁርጠኝነት ሊታገሉ ይገባል አለ የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ፡፡

ስምረት ፓርቲ ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች የጨካኙን ቡድን ዕድሜ ለማሳጠር የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡

ህገ ወጡ ህወሓት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከማፍረስ ባለፈ ዋነኛ የውጭ ሃይሎች ጉዳይ አስፈፃሚ በመሆን የትግራይ ምድርን ሲኦል እያደረገ ይገኛል፡፡

ህገ ወጥ ቡድኑ ከመነሻው ጀምሮ የፕሪቶርያው ስምምነት እንዳይተገበርና የሰላም ሒደት እንዳይጠናከር እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን መግለጫው አስታውሷል፡፡

ሕገ ወጡ ሕወሓት ከግላዊ የቡድን ጥቅም ውጭ ለሕዝብ ጥቅም ምንም አይነት ዓላማ እንደሌለው በተግባር የተረጋገጠ ሐቅ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

በአሁኑ ሰዓት እያደረገው የሚገኘው የጦርነት ጉሰማም ቡድኑ ለራሱ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም የማይሰራ መሆኑን ዋናው ማረጋገጫ እንደሆነ ነው ያመላከተው፡፡

ይህ የሰላም ፀር ሃይል ስልጣን ከጊዜያዊ መስተዳደር በሃይል ከያዘ በኋላ በሻዕቢያ የተሰጠው ትእዛዝ ለመተግበር አፋኝ እና ጸረ ሕዝብ ሕጎችን በማውጣት ግላዊ ጥቅሙን ለማሳካት ወደ ሙሉ አፋኝ ሥርዓት ገብቷል ብሏል፡፡

ወጣቶችን በግድ እያፈሰ ወደ ጦርነት እያጋዛቸው ነው ያለው ስምረት ፓርቲ ÷ በዚህ የተነሳ የትግራይ ወጣትን በመሬቱ እና ሀገሩ መግቢያ መውጫ አሳጥቶ የትግራይ ክልልን ወጣት አልባ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

ሕገ ወጡ ህወሓት በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን አፈሳ እና ግድያ በሕግ ፊት ተጠያቂ ለማድረግ ዜጎች እያንዳንዱን ማስረጃ ሊይዙ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ተደራጅተው በመታገል የጨካኙን ቡድን ዕድሜ ለማሳጠር የተጀመረውን ትግል አጠናክረው እንዲቀጥሉም ስምረት ፓርቲ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የፌዴራል መንግሥት እና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ይህንን ጸረ ሰላም ቡድን ለማስወገድ እና ወደ ሕግ ለማቅረብ ለሚደረገው ትግል ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቋል፡፡