አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት መሪነት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ከኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ ዓለምን በፍጥነት እየቀየረ ያለውን የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት እየገነባች ትገኛለች።
ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገብ ተችሏል።
በዚህ የዲጂታላይዜሽን ጥረት ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የዲጂታል መሰረተ ልማትና የቴሌኮም ዘርፍ ሪፎርም፣ የ4ጂ እና 5ጂ ኔትዎርክ መስፋፋትና የዳታ ማዕከላት ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የቴሌኮም ዘርፉ ለግል ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ኩባንያዎች እንዲሰማሩና የስልክ እንዲሁም የኢንተርኔት ተደራሽነትና ጥራት እንዲሻሻል አስችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የ4ጂ ኔትዎርክ ዝርጋታ ከ1 ሺህ 200 በላይ ለሆኑ ከተሞች የተዳረሰ ሲሆን፤ 82 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኗል።
የ5ጂ ኔትዎርክ አገልግሎት ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ በ33 ዋና ዋና የክልል ከተሞች ተጀምሯል።
የፋይናንስ ቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ክፍያ ከፍተኛ እመርታ ታይቶበታል፡፡
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና በብሔራዊ መታወቂያ ፋይዳ ፕሮግራሞች ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆኑ ስራዎች ተሰርተዋል።
የመንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል ስርዓት ተደራሽ በማድረግ ረገድ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
ወጣቶችን በኮደርስ ስልጠና በማብቃት በዘርፉ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ሲሆን፤ በአፍሪካ የመጀመሪያው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ግንባታም እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የዲጂታል ስርዓት የሚተገበርበት መመሪያና የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ የግል መረጃ ጥበቃ እና የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ አዋጆች ወጥተው ስራ ላይ ውለዋል።
በአሁኑ ወቅት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን፤ ይህም የመጀመሪያውን ምዕራፍ ስራዎች ተደራሽነት በማጠናከር ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ተግባራት ላይ ያተኮረ ነው።
በቴዎድሮስ ሳህለ