ፋና ስብስብ

በመደመር መንግሥት የጋምቤላ ክልልን የቱሪዝም ሃብት የማጠናከር ሥራ

By tigist gizachew

August 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልልን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት በማልማት የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ አለ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ።

የመደመር መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ የትናንት የታሪክ ሀብታችንን፣ የዛሬውን ልማታችንን እና የነገውን ብልጽግናችንን በማቀናጀት ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ግብ አለው።

የጋምቤላ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ኮንግ ሬት እንዳሉት÷ በክልሉ ያለውን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት የማልማት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

በተለይም በክልሉ እምቅ የብዝሃ ሕይወት ሃብት ያለውን የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ከአፍሪካ ፓርክስ ኔትወርክ ጋር በመቀናጀት ለማልማት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በፓርኩ የሚገኙት የዱር እንስሳት የክረምትና የበጋ እንቅስቃሴያቸውን መሠረት ያደረገ የመዳረሻ ቦታዎችን ለማልማት በአውሮፕላን የታገዘ የቅኝት፣ የሰርቬይና የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በባዮስፌር የተመዘገቡትን የተፈጥሮ ደኖችን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መስህቦችን ለማልማት የጥናትና ልየታ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በቢሮው የቱሪዝም መዳረሻ መሠረተ ልማት ቡድን መሪ አቶ ደርባቸው ሸዋለም በበኩላቸው÷ በክልሉ 109 የቱሪዝም መስህቦችን በጥናት በመለየት እንደየ ሀብት አቅማቸው በቅደም ተከተል ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በተለይም ከፍተኛ የቱሪዝም አቅም ያለውን የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ያለበትን የመሠረተ ልማት ተግዳሮት ለመፍታትና የዘርፉን ሀብት በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል ከአፍሪካ ፓርክስ ኔትወርክ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በፓርኩ አቅራቢያ በሚገኘው በአሌሮ ግድብ ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ሎጆች ለመገንባት የግንባታ ግብዓቶች መቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡