የሀገር ውስጥ ዜና

የምክክር ጉባዔው ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ አጀንዳዎቻቸው ላይ በጋራ የሚመክሩበትን ዕድል ፈጥሯል

By tigist gizachew

August 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ አጀንዳዎቻቸው ላይ በጋራ የሚመክሩበትን ዕድል ፈጥሯል አሉ ተመካካሪዎች፡፡

በኢትዮጵያን ለዘመናት ሲፈትኗት የቆዩ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር ለመፍታት የሚያስችል እድል ተፈጥሯል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተመካካሪ ቄስ ተሻለ አለባቸው እንዳሉት ÷ ጉባዔው በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በስፋት እየመከረ ነው፡፡

በየደረጃው ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የታደሙበት፣ የሀሳብ ብዝሃነት የሚስተናገድበት አካታችና አሳታፊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምክክሩ ለዘመናት የኢትዮጵያውያን የልዩነት ምንጭ ሆነው የዘለቁ አጀንዳዎችን የያዘ መሆኑን ገልጸው÷ ለሀገር የሚበጁ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጀመረው ምክክር ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ ተሞክሮ እንደሚወሰድበት አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በዓድዋና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የጻፍነውን አኩሪ ታሪክ በምክክሩ ላይ በመድገም ለትውልድ አሻራ አስቀምጠን እናልፋለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ተመካካሪ ድንቅነሽ ኡባራ በበኩላቸው÷ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተመካካሪዎች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የየራሳቸውን ሀሳብ ማንጸባረቃቸውን ጠቁመው÷ በጉባዔው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሚቻል አመላክቷል ብለዋል፡፡

ጉባዔው ዜጎች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር የሀገር ሁለንተናዊ ልማት እንቅፋቶችን በማለፍ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ የሚያስችል ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ ተመካካሪ አበራሽ አባይነህ ናቸው፡፡

ተመካካሪዎች መደማመጥን መርሐ በማድረግ ለምክክር በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሀሳቦችን መሰንዘራቸውን አውስተው÷ ሀገርን የሚያጸና መፍትሔ እንደሚመጣ ተስፋ ሰንቄያለሁ ብለዋል፡፡