የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ በጋራ የመልማት ስንቅ ፤ የባሕር በር

By Melaku Gedif

August 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተፈጥሯዊ እና ጂኦ ፖለቲካዊ እውነታዎች የሀገራትን የወደፊት እጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የባሕር በር ማጣቷ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቷና ለቀጣናዊ ደህንነቷ ትልቅ ፈተና ነው።

የኢኮኖሚ ዕድገት መሻት እና የጂኦ ፖለቲካዊ ህልውና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን በግልጽ እና በቁርጠኝነት ወደ መድረክ በማምጣት ማንሳቱ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ የሕልውና እና የመልማት ፍላጎትን ለማረጋገጥ የተወሰደ አስፈላጊና ወቅታዊ ርምጃ ነው።

ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ወደብ አልባ ሀገራት መካከል በሕዝብ ቁጥር ትልቋ ናት።

ሀገሪቱ ለገቢና ወጪ ንግድ በየዓመቱ የምታወጣው የቢሊየኖች ዶላር የባሕር በር ኪራይ ክፍያ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

ይህም የባሕር በር ጥያቄዋ የቅንጦት ሳይሆን የሀገር ሕልውና እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዋስትና ጉዳይ ያደርገዋል፡፡

የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ የሉዓላዊነት ጥሰት ወይም የጎረቤት ሀገራትን ጥቅም የመጋፋት ፍላጎት ሳይሆን በጋራ የመልማት መርሕን የተከተለ ነው፡

የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ህግ ኮንቬንሽን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ወደብ አልባ ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ እና የባሕር ሃብቶችን የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋሉ።

ኢትዮጵያ ይህንን ህጋዊ መብቷን እና ታሪካዊ ድርሻዋን በመረዳት ጥያቄዋን በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ በማቅረብ የጋራ ልማት እና የጋራ ተጠቃሚነት በመጠየቅ ላይ ትገኛለች።

የባሕር በር ተጠቃሚነት ጥያቄዋም ዲፕሎማሲያዊ እና የጋራ ተጠቃሚነትን ያስቀደመና ድርድርን መሠረት ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ያሏት በርካታ የልማት ፀጋዎች እንደ ታዳሽ ኃይል ፤ የአየር መንገድ አገልግሎት፣ የግብርና ምርቶች እና ሰፊ የሀገር ውስጥ ገበያ ለጎረቤት ሀገራት ታላቅ በጋራ የመልማት ዕድል ይዘው ይመጣሉ።

የረጅም ጊዜ የጋራ ልማት ስምምነት ማድረግ የኢትዮጵያን ጥያቄ ከመመለሱም በላይ፣ የወደብ ባለቤት ሀገራትን ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል።

ሀገራት በኢኮኖሚ እርስ በርስ በሚተሳሰሩበት ወቅት በቀጣናው ያለው ውጥረት ይቀንሳል፤ በምትኩም ሰላም፣ ውህደት እና የጋራ ብልፅግና ይረጋገጣል።

በፍትሃዊ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አመክንዮዎች በጋራ መልማትን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ዘላቂ ሠላም እና ዕድገት መሠረት ይጥላል።

በምሕረት ደምሴ