የሀገር ውስጥ ዜና

ችግኝ ብቻ ሳይሆን ተስፋን የምትተክል ከተማ

By Melkam Fekadu

August 14, 2026

አንድ ከተማ የምትመዘነው ለነገ ትውልድ በምትተወው ዘላቂ ልማት፤ በምትጠብቀው ተፈጥሮ እና ዛሬ በምትተክለው ችግኝም ጭምር ነው። ‎ ‎አዲስ አበባም በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ በየዓመቱ ነዋሪዎቿን በነቂስ በማሳተፍ፣ የከተማዋን መሬት በአረንጓዴ ለመሸፈን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጥላ፣ የውበት እና የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከል የከተማዋን መልክ በቀስታ ግን እጅግ ውብ በሆነ መልኩ መቀየር ጀምራለች። ‎ ‎ይህ ጉዞ የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ለማሳደግ አስችሏል። ‎ ‎በዚህ ውስጥ ትናንት የቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች ዛሬ በአረንጓዴ ሲተካ፣ ትናንት በፀሐይ የሚያቃጥሉ ቦታዎች ዛሬ ጥላ ሲኖራቸው፣ ትናንት የማይታሰብ የከተማ ውበት ዛሬ የነዋሪዎቿ ዕለታዊ ሕይወት አካል እየሆነ ሲመጣ የሚታየው ለውጥ በቁጥር ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን ነው። ‎ ‎በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አዲስ አበባ በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የከተማ አረንጓዴነትን ከውበት በላይ ወደ የአየር ጥራት፣ የአካባቢ ጤና፣ የሕዝብ መዝናኛ፣ የከተማ ሙቀት ቅነሳ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የነገ ትውልድ የኑሮ ጥራት ጉዳይ እያሸጋገረችው ነው። ‎ ‎እናም የዛሬው አዲስ አበባ ችግኝ ለመትከል ብቻ የምትወጣ ከተማ አይደለችም፤ የነገውን አዲስ አበባ በዛሬ እጆቿ ለመገንባት የምትተጋ ከተማ ናት። ‎ ‎እንደ ከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ከቀናት በፊትም በአንድ ጀምበር 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞችን መትከል የሚለው ጉዞ ተጨማሪ መልዕክቱ ቁርጠኝነቷን ነው፡፡ ‎ ‎ሰው ከተፈጥሮ እየታረቀ ከአየር ጋር፣ ከውሃ ጋር፣ ከአፈር ጋር እና ከተፈጥሮ ጋር በሰላም የሚኖርባትን ከተማም በመፍጠር ላይ ናት። ‎ ‎አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መዲና ብቻ አይደለችም፤ አፍሪካን ከዓለም ጋር የምታገናኝ ከተማ ናት። ‎ ‎ስለዚህ የከተማዋ ውበት፣ ንፅህና፣ አረንጓዴነት፣ የመኖሪያ ምቾት እና የከተማ አቀራረብ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይም ይሆናል። ‎ ‎ስለዚህ አዲስ አበባን አረንጓዴ፣ ንፁህ፣ ውብ፣ ዘመናዊ እና ለመኖር ምቹ ከተማ ማድረግ የከተማ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የሀገር ገጽታ ግንባታም ነው። ‎ ‎ዛሬ የምንተክለው ዛፍ ነገ እኛ በጥላው ስር ለመቀመጥ ብቻ አይደለም፤ ልጆቻችን እና የልጆቻችን ልጆች በንፁህ አየር እንዲተነፍሱ፣ በአረንጓዴ ከተማ እንዲኖሩ፣ በውብ አካባቢ እንዲያድጉ የምናስቀምጠው የተስፋ ፊርማ ነው። ‎ ‎ችግኝ ስንተክል ዛፍ ብቻ አንተክልም፤ ጥላ እንተክላለን፣ ንፁህ አየር እንተክላለን፣ ውበት እንተክላለን፣ ምግብ እንተክላለን፣ ተስፋን እንተክላለን፣ ለነገ ትውልድም ሕይወት እንተክላለን። ‎ ‎አዲስ አበባ የምትተክለው ችግኝ ቁጥር ብቻ አይደለም፤ የተለወጠ አስተሳሰብም ጭምር ነው ። ዛሬ የምትንከባከበው ዛፍ ነገ የሚያርፍበት ትውልድ ነው።