የሀገር ውስጥ ዜና

የሕገ ወጡ ህወሓት የወጣቶችን ተስፋ የማምከን ጉዞ

By Mikias Ayele

August 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ማሕበረሰብ ህልውና፣ ተስፋ እና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚለካው በወጣቶቹ የሥራ ተነሳሽነት፣ በፈጠራ ክህሎታቸው እንዲሁም ሀገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር በሚያሳዩት ጉልበት ነው።

በትግራይ ምድር ግን ይህ ተፈጥሯዊ እውነት ተገልብጦ ወጣቱ የጦርነት ማገዶ አረጋውያኑ ደግሞ የልጆቻቸውን አስከሬን ተቀባይና የቀብር አስፈፃሚ ሆነዋል።

ራሱን የክልሉ ተሟጋች አድርጎ የሚስለው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይን ወጣት ዳግም ወደ እልቂት አዙሪት ለመክተት እያደረገ ያለው እኩይ ተግባር የማህበረሰቡን ስነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መሰረት በከፍተኛ ሁኔታ እየናደው ይገኛል።

ቡድኑ ስልጣንና የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሁልጊዜም የሚጠቀመው የፍርሃትና የፅንፈኝነት ትረካ በመሆኑ ለዘመናት በትግራይ ህዝብ ላይ የጫነውን የድህነትና የጦርነት ቀንበር ለማስቀጠል ወጣቱን ከትምህርት ገበታ፣ ከፈጠራ እና ከእርሻ ስራው ነጥቆ ወደ ጦር ግንባር እየነዳው ይገኛል።

ይህ ተግባር ወጣቱን መማገድ ብቻ ሳይሆን የነገዋን ትግራይ መሪዎች፣ መሃንዲሶች እና ሀኪሞች አስቀድሞ የማምከን ስራ ነው።

ቡድኑ ወጣቱን ለጦርነት ለመማገድ የሚጠቀመው የማስገደጃ ስልት እጅግ ረቂቅ ከመሆኑ የተነሳ በጦርነት የማይሳተፍ ቤተሰብን ማህበራዊ አገልግሎት መከልከልና ማግለልን፣ ክልሉ ሁልጊዜም በከበባ ውስጥ እንዳለች አድርጎ በሀሰት ትረካ መስበክን እና እርዳታንና መሰረታዊ አቅርቦቶችን ለታጣቂ ቤተሰቦች ብቻ ቅድሚያ በመስጠት ወጣቱን አማራጭ ማሳጣት ማቀፉ የጭካኔውን ልክ ያሳያል።

ከዚህም በተጨማሪ ይህ አፍራሽ አካሄድ በትግራይ ምድር ላይ ያስከተለው የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ትስስር መላላት በቀላሉ የሚጠገን ባለመሆኑ ወጣቱ ሃይል አምራችና ታታሪ ከመሆን ይልቅ የጦርነት አውድማዎችን እንዲናፍቅ እና በጠመንጃ ኃይል ብቻ እንዲያምን ተደርጎ የስነ-ልቦና ስብራት እየደረሰበት ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ የንግድ፣ የእርሻ እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ሙሉ በሙሉ እንዲቀጭጩ እና ህዝቡ በቋሚነት የዕለት እርዳታ ጠባቂ እንዲሆን የተደረገው ይኸው ስብስብ የሰው ኃይሉን ለልማት ከመጠቀም ይልቅ ለፖለቲካ ቁማር ማጫወቻነት መምረጥ ስላስደሰተው ብቻ ነው።

ከትውልድ ወደ ትውልድ መሻገር የነበረባቸው በጎ ባህላዊ እሴቶች፣ የትህትና እና የክብር መገለጫዎች በጦርነት ፕሮፓጋንዳ እየተተኩ በመሆናቸው፣ ነገ ክልሉን ተረክቦ በሰላማዊ መንገድ የሚያስተዳድር ንቁ እና ብቁ ዜጋ የማፍራቱ ሒደት ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በትግራይ ወጣቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ይህንን አስገዳጅ የክተት ምልመላ እና የስነ-ልቦና ጭቆና ዝም ብለው መመልከታቸው የቡድኑን እኩይ ተግባር ይበልጥ እንዲቀጥል አደፋፍሮታል።

ወጣቶች የራሳቸውን ሕይወት የመምራት፣ የመማር እና የመስራት መብታቸው በጠብመንጃ አፈሙዝ እየተነጠቀ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ድርጊቱን በግልጽ አለማውገዝና በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ግፊት አለማድረግ በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ዘላቂ ውድመት እውቅና የመስጠት ያህል ይቆጠራል።

ስለዚህም ይህንን ግልጽ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በማጋለጥ ወጣቱ ከዚህ የባርነት እና የሞት አዋጅ የሚላቀቅበትን መንገድ መፈለግ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል።

በመጨረሻም ይህ የህገ ወጡ ህወሓት የሞት አዙሪት በአስቸኳይ ሊቆም የሚገባው በመሆኑ የትግራይ ወጣቶች ለሕገ ወጡ ህሕወት ጥቂት የቡድኑ መሪዎች ስልጣን መቆያ ማገዶ ላለመሆን መስራት አለባቸው፡፡

ክልሉ የወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ እንዲሆኑ የክልሉ ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች ይህንን ህገ ወጥ ስብስብ “ይበቃል!” በማለት የወጣቶችን የወደፊት ተስፋ ከጥፋት ሊታደጉ ይገባል።

በሃይለኢየሱስ መኮንን