የሀገር ውስጥ ዜና

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሰላምና ደህንነት ችግሮችን ለመፍታት ያለመው ጉባዔ

By Mikias Ayele

August 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 36ኛው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የፖሊሲ አካላት ጉባዔ በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጉባዔው የሁሉም አባል ሀገራት ከፍተኛ ኤክስፐርቶች፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች፣ የመከላከያ ሚኒስትሮችና ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

በመድረኩ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚስተዋሉ የሰላምና የደኅንነት ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የግማሽ የበጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀሙን በመገምገም የተጠንቀቅ ኃይሉ የቀጣናው ቁልፍ የሰላምና የደኅንነት ተቋም እንዲሆን የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

ኢትዮጵያን በመወከል በጉባዔው የተሳተፉት ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ÷ አባል ሀገራት የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይልን በማጠናከር ረገድ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የተጠንቀቅ ኃይሉ እየተገበረ ያለውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም ኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን በማስገንዘብ አባል ሀገራቱ ለአጀንዳው ስኬታማ ትግበራ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሰላምና የደኅንነት ሁኔታን ለማጠናከር የምታደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን የመከላከያ ሰራዊት ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡