የሀገር ውስጥ ዜና

 ፈተናዎችን በመቅረፍ ከችግር አዙሪት ወደ ዘላቂ ብልጽግና የመሸጋገር ጉዞ

By Mikias Ayele

August 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ወደላቀ ከፍታና ብልጽግና ለመሸጋገር በምታደርገው ጉዞ የሚገጥሟትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጋሬጣዎች በቆራጥነት በማሸነፍ ትገኛለች፡፡

በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን እየፈተኑ ያሉትን ዋና ዋና ሰው ሠራሽና መዋቅራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የመደመር መንግሥት ሁለንተናዊ ሪፎርም በማካሄድ ላይ ነው።

በተለይም የኑሮ ውድነትን፣ ሌብነትን፣ ዋልታ ረገጥ መንደርተኝነትንና የጠባቂነት ሥነ ልቦናን በዘላቂነት ለመቀነስ በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩት የተቀናጁ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ነው።

የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል መንግሥት መጠነ ሰፊ የገበያ ማረጋጊያ ስልቶችን እየተገበረ ይገኛል።

ይህንንም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የግብይት ማዕከላትን በማስፋፋትና የቀጥታ ትስስርን በመፍጠር እውን እያደረገው ነው፡፡

በሀገር ውስጥ በስፋት የተጀመረው የስንዴና የሌማት ትሩፋት ምርት የውጪ ጥገኝነትን ከመቀነሱ በላይ የገበያ አቅርቦትን እያሳደገ ነው።

በሌላ መልኩ ደላላን በማስቀረት አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ የቅዳሜና የእሑድ ገበያዎች፣ ትላልቅ የገበያ ማዕከላትና የሸማቾች ማኅበራት ማዕከላት በስፋት እንዲስፋፉ ተደርጓል።

ሌብነትና የሕዝብን ሀብት ያለአግባብ መመዝበር የሀገርን ዕድገት ወደኋላ የሚጎትቱ ዋነኛ ጠላቶች በመሆናቸው፣ መንግሥት ሌብነትን ያለመታገስ ፖሊሲን እየተከተለ ነው።

ይህንንም የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግና ከሰው ንክኪ በማውጣት የሙስና ዕድሎችን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ቁርጠኝነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል።

በሕዝብና በሀገር ሀብት ላይ አላግባብ የሚበለጽጉ አካላትን በሕግ የመጠየቅና ሥርዓት የማስያዝ ሥራዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ከአመለካከትና ከሥነ-ልቦና አንጻር ሀገራዊ አንድነትን የሚሸረሽረውን ዋልታ ረገጥ እና የተረጂነት ሥነ-ልቦናን ለመቀየር ሰፊ የዕሳቤ ለውጦች እየተሠሩ ነው። በዚህ ላይ በተሠራው ሥራ ሀገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊ ስሜት እየጨመረ መጥቷል፡፡

ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ሁልጊዜ ከመንግሥት ድጋፍ የመጠበቅን ጎጂ ባህል ወደ አምራችነት የመቀየር ሥራ ውጤት እያመጣ ነው።

በአጠቃላይ መንግሥት የኑሮ ውድነትን፣ ሌብነት፣ መንደርተኝነትንና ጠባቂነትን ለመቀነስ እና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየሠራ ነው፡፡

ይህ ጉዞ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል።