የሀገር ውስጥ ዜና

 የምክክር ጉባዔው አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ሀገራዊ መግባባትን የሚያጠናክር ነው – ተመካካሪዎች

By Mikias Ayele

August 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ሀገራዊ መግባባትን የሚያጠናክር ትልቅ መድረክ ነው አሉ ተመካካሪዎች።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

ተስፋዬ ደጀኔ የተባሉ ተመካካሪ ÷ በሀገሪቱ አዲስ ምዕራፍ የከፈተው የሀገራዊ ምክክር ሒደት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል፡፡

ምክክሩ ለቆዩ ችግሮች በጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ ያስቻለ አዲስ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን  አመላክተዋል፡፡

በምክክሩ በርካታ ትምህርቶች የተወሰዱ ሲሆን÷ ለነበሩ ችግሮች በርካታ የመፍትሔ ሀሳቦች መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ የሀገራዊ ምክክር ሒደት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ ወደ ትልቅ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው ብለዋል፡፡

ሌላኛው ተመካካሪ ኢብሳ ኢብራሒም በበኩላቸው÷ የምክክር መድረኩ ሒደት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውና አዎንታዊ እንደሆነ ገልጸው÷ ይህም ሀገራዊ መግባባትን የሚያጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክሩ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በስፋት ያሳተፈ በመሆኑ ሂደቱ የተሟላ እና አካታች መሆኑን የገለጹት ደግሞ ተመካካሪ ቦጋለ ሰይዳ ናቸው፡፡