የሀገር ውስጥ ዜና

የሶላር ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

By emebet sisay

August 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶላር ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር።

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ቁንቢ ወረዳ በሀሮ ጉራቲ እና በሀሪሮ አካባቢዎች የተገነቡት የፀሐይ ኃይል (ሶላር) ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።

ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን÷ የአካባቢው ነዋሪዎች ባገኙት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የሀሪሮው ፕሮጀክት ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም ሌሎች ተቋማትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል።

በ640 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡት ፕሮጀክቶቹ በአጠቃላይ 800 ኪሎ ዋት የፀሐይ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸው ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት 477 አባወራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን÷ ፕሮጀክቱ 3 ሺህ 646 አባወራዎችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም እንዳለው ተገልጿል።

አዲሱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የአካባቢውን ነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግና የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተመላክቷል።

በዘቢብ ተክላይ