ስፓርት

የባሕር ዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚያስችለውን የካፍ ፍቃድ አገኘ

By tigist gizachew

August 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር ዳር ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዝቅተኛ መመዘኛ በማሟላት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚያስችለውን ፍቃድ አግኝቷል፡፡

የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጋሻው ተቀባ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ የካፍን መስፈርቶች በመከተል ስታዲየሙ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ እንዲሆን በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በተለይም የተጫዋቾች ማረፊያ ክፍል ደህንነት፣ የልዩ እንግዳ ቦታዎች (ቪ አይ ፒ) ደህንነትና የሜዳ ጥራት በከፍተኛ ትኩረት የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጪው መስከረም ወር ከሴኔጋል ጋር የሚያደርገው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ መርሐ ግብር በዚሁ ስታዲየም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የፊፋ እና የካፍን ተጨማሪ መስፈርቶች ለማሟላት የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡

ስታዲየሙ የካፍን ዝቅተኛ መመዘኛ በማሟላት ያገኘው ፍቃድ ለስፖርቱ እድገት እና ለአካባቢው የቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡