የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ ለቀጣናው የጋራ ብልጽግና መሰረት ነው

By Hailemaryam Tegegn

August 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላትና በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄዋ በምኞት ብቻ የሚቀር አይደለም።

ኢኮኖሚና መጻዒ ዕድል ሁልጊዜም የተሳሰሩ በመሆናቸው የባህር በር ወሳኝና አስገዳጅ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ በጀመረችው አስደናቂ ትጋት የኢንዱስትሪዋ መስፋፋት፣ የግብርና ምርትና ምርታማነቷ ማደግና የኃይል ምርቷ ከፍ ማለት ትልቅ እመርታ ነው፤ ነገር ግን የባህር በር አልባ ሆና መቆየቷ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ይገድበዋል።

ሀገሪቱ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ በሴራ የባህር በሯን ካጣች ወዲህ ከ90 በመቶ በላይ የወጭ ንግዷ በዋናነት በወደብ ኪራይ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ወጪ ዳርጓት ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለወደብ ክፍያና ለሎጂስቲክስ ወጪ ብቻ በዓመት የምታወጣው ቢሊየን ዶላሮች ለጤና እና ትምህርት ተቋማት እንዲሁም ለበርካታ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ቢውል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚችል ነው።

በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ ኢኮኖሚዎች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ ሆና መቀጠሏ ሀገር በቀል ላኪዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ማነቆ ይሆናል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ወደ ሥራው ዓለም ለማስገባት ከፍተኛ የሥራ እድል ፈጠራ ተግባራት ይጠበቃሉ፡፡

በዚህ ረገድ ኢንዱስትሪውን ማስፋፋትን ጨምሮ ለሥራ እድል ቁልፍ የሆኑ የልማት ስራዎች ለመከወን የባህር በር ወሳኝ ጉዳይ ነው።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ የምታነሳውን አንገብጋቢ ጥያቄ በማጣመም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት በርካታ መሰረተ ቢስ ውንጀላዎች ሲሰራጩ ይስተዋላል።

እውነታው ግን ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት የሚጋፋ ወይም ግጭት የሚቀሰቅስ ሳይሆን ለቀጣናው የጋራ ልማት የሚበጅ አዲስ መንገድ ነው፡፡

ይህም ከሀገሪቱ የልማት ግስጋሴ አንጻር የቀጣናውን ሰፊ የባህር ዳርቻዎች ወደ ኢኮኖሚ ሀብትነት ለመቀየር የሚያስፈልገውን ትክክለኛ የንግድ አቅምና ኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚያረጋግጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባህር በር አልቦነት የመጣው ከተፈጥሮ ጂኦግራፊ ሳይሆን ከታሪካዊ ስህተቶችና ከባለፈው ዘመን የውስጥ መከፋፈሎች መሆኑን አስምረውበታል።

እነዚህን የታሪክ ስህተቶች በዲፕሎማሲና በኢኮኖሚ ውህደት ማረም ለወደፊቱ ትውልድ የሚከፈል ግዴታ ነው።

ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ዳግም ማግኘቷ ለመላው ቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት ታሪካዊ ሚናዋን ያጠናክራል፡፡

ኢትዮጵያ የምታቀርበውን የወንድማማችነት፣ የንግድና የጋራ እድገት ጥሪ መቀበል፤ ቀጣናውን ወደተሳሰረ የኢኮኖሚ መደለድል የሚያሸጋግር ነው፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነትን በጋራ ልማት መርህ ማረጋገጥ በመላው የአፍሪካ ቀንድ ለሚገኙ ሀገራት በሙሉ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴን ይፈጥራል።

በምሕረት ደምሴ