የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው – አሜሪካ

By Hailemaryam Tegegn

August 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው አሉ የአሜሪካ መከላከያ ልዑካን፡፡

መነሻውን ከሮድ አይላንድ ያደረገው የአሜሪካ መከላከያ ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከል ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።

ስልጠናው ሁለቱ ሀገራት በወታደራዊ መስክ በትብብር ለመስራት ያደረጉትን ስምምነት መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን፥ በወታደራዊ ተልዕኮዎች ወቅት በሰብዓዊ መብቶችና ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ሕጎች አጠባበቅ ላይ ያተኮረ ነው።

በመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት የሥልጠና ዳይሬክተር ሌተናል ኮሎኔል ምናሴ ኃይሉ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው እየፈጠረች ባለው መልካም ተፅዕኖ ተሰሚነቷ እያደገ መጥቷል።

ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን አለመረጋጋት ለመፍታት ያለ ኢትዮጵያ ማሳካት እንደማይቻል በመረዳታቸው ለጋራ ተጠቃሚነት ከኢትዮጵያ ጋር እየሠሩ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች በምትወጣቸው ግዳጆች በተለይም በፈንጅ አወጋገድና በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ወቅት በሰብአዊ መብትና ዓለም አቀፍ ሕጎች አጠባበቅ ዙርያ አዲስ ዕውቀት የሚፈጥር ሥልጠና መሆኑን ተናግረዋል።

ሥልጠና መስጠት ብቻ ሳይሆን እኛ ጋር ያለውን የካበተ ልምድ ይወስዳሉ ነው ያሉት፡፡

የሥልጠና ልዑኩ አስተባባሪ ሌተናል ኮሎኔል ዛከሪ ማካርተር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም ለሶማሊያ ሠላምና መረጋጋት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑን አውስተው፥ ሥልጠናው የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።