አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሙስና ወንጀልን በዘላቂነት ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል አለ ፍትሕ ሚኒስቴር።
በሚኒስቴሩ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክተር ምስክር ታሪኩ እንዳሉት ÷ በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ሺህ 600 በላይ የሙስና ወንጀል መዝገቦች ተመርምረው ከ300 በላይ ክሶች ተመስርተዋል፡፡
በዚህም ከ400 በላይ ተከሳሾች በፍ/ቤት ቀርበው እንዲቀጡ መደረጉን ጠቁመው÷ በተጠቀሱት መዝገቦች ውስጥ አንድ መዝገብ እስከ 30 እና 40 ተከሳሾችን ሊያካትት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በሒደቱ የተወሳሰቡ የሙስና ወንጀል ጉዳዮችን በማጣራት ተገቢው ውሳኔ መስጠት መቻሉን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
ከተመረመሩት መዝገቦች ውስጥ ከ300 በላይ በሚሆኑት ላይ ክስ የመመስረት ሥራ መከናወኑን አንስተው ÷ የሙስና ወንጀሎችን በሕግ አግባብ ወደ ፍርድ ሒደት የማስገባት ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል።
ይህም የሙስና ወንጀልን በሕግ ለመቆጣጠር እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተወሰደውን ርምጃ እንደሚያሳይ አመልክተዋል፡፡
ሙስናን መከላከልና መቆጣጠር የአስፈጻሚ አካላት ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆነ ጠቁመው ÷ የሕግ አውጪው ተገቢውን ሕግ በማውጣት፤ የሕግ ተርጓሚው ደግሞ ሕጉን በተገቢው መንገድ በመተርጎምና በማስፈጸም የሙስና ትግሉን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።
የሙስና ወንጀልን በመከላከል፣ በመመርመርና ተጠያቂነትን በማስፈን ሒደት ሁሉም የሕግ ተቋማት ተገቢውን ትኩረትና ኃላፊነት በመውሰድ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት