የሀገር ውስጥ ዜና

የባሕር በር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትብብርና በቁርጠኝነት መስራት ይገባል – የመዲናዋ ነዋሪዎች

By emebet sisay

August 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በራችንን ያለ አግባብ ያጣንበት መንገድ ቁጭት ይፈጥራል አሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፡፡

ለፋና ዲጂታል አስተያየታቸውን የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች÷ ለእኛ ብቻ ሳይሆን መጪው ትውልድ የባሕር በር ባለቤት እንዲሆን በቅንጅት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተዋቸው መኮንን እንዳሉት ÷ እንደ ሀገር በጋራ እና በቅንጅት በመስራት ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ ለመሆን የጀመረችውን ጥረት ማጠናከር ይገባል፡፡

የባሕር በር ያጣንበት መንገድ ቁጭት ፈጥሮብናል፤ እንደ ሀገር ሁሉም የድርሻውን በመወጣት የባሕር በር የምናገኝበትን መንገድ ማፋጠን አለብን ብለዋል፡፡

አቶ ዮናስ ተዘራ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ባለመሆኗ በዓመት ብዙ ቢሊየን ዶላር ወጪ እያወጣች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እያከናወነው ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በማጠናከር እና ዜጎችም የድርሻቸውን በመወጣት የባሕር በራችን እንዲመለስ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የባሕር በር ያላቸው ሀገራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ ዘመኑ አበበ የተባሉ የመዲናዋ ነዋሪ ናቸው፡፡

የባሕር በር ያላቸው ሀገራት በሥራ እድል ፈጠራ እና በሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሰፊ እድል እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡

ስለሆነም ዓለም አቀፍ ልምዶችና ተሞክሮዎችን በመጠቀም የባሕር በር ባለቤት መሆን የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በትዕግስት ግዛቸው