አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ለ2019 በጀት ዓመት የሥራ ማስፈጸሚያ የሚውል ከ18 ነጥብ 57 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አጸድቋል። የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ኡማን አሙሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በክልሉ ወጪዎችን በራስ የገቢ ምንጭ ለመሸፈን አበረታች ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ለ2019 በጀት ዓመት ከተያዘው አጠቃላይ በጀት ውስጥ ከ11 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነውን በክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ ለመሸፈን መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡ ቀሪው 7 ቢሊየን ብር ከፌደራል መንግስት በድጎማ የሚገኝ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ የገቢ አቅሞችን በመጠቀም ገቢን ለማሳደግ የተጀመሩ አበረታች ጥረቶችን ማጠናከር እንደሚገባ የምክር ቤቱ አባላት አስገንዝበዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተያዘው በጀት የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲውል በየደረጃው ክትትል ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡