የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ – የምሥራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል

By Hailemaryam Tegegn

August 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና የታዳሽ ኃይል ልማት እያካሄደች ነው፡፡

በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም ስነ ምህዳር በመፍጠር ረገድ አስደናቂ እመርታ እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡

ሙሉ ለሙሉ በሕዝብ ሀብትና ርብርብ ተገንብቶ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዚህ ታላቅ የስኬት ጉዞ ማዕከል ነው፡፡

ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ማመንጨት አቅም በእጥፍ በማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግድቡ የምረቃ ስነስርዓት ወቅት ባደረጉት እንዳሉት፥ የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም የመፈጸም አቅምና ጽናት እንዳላት በተግባር ያሳየችበት የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል ማመንጫዎች ባሻገር የታዳሽ ኃይል ምንጭ አማራጮቿን ለማስፋት በንፋስ፣ በፀሐይ (ሶላር) እና በከርሰምድር እንፋሎት (ጂኦተርማል) ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች፡፡

በንፋስ ኃይል ልማት ረገድ የ120 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ (80 ሜጋ ዋት) ተጠናቅቆ ወደ ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል ተቀላቅሏል፡፡

በተጨማሪም ከአሸጎዳ እና ከአዳማ የንፋስ ፓርኮች ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱ የታዳሽ ኃይል አማራጮች እንዲሰፉ አስችሏል፡፡

እንደ ቱሉ ሞዬ እና አሉቶ ላንጋኖ ያሉ የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ደግሞ ሀገሪቱ ካላት ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያደርጉ የታዳሽ ኃይል ተደማሪ አቅሞች ናቸው፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች የተዘረጉ የጸሀይ ኃይል ማመንጫዎችና ከብሔራዊ ግሪድ ውጪ ያሉ አነስተኛ የጸሀይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የገጠሩን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት እያሳደጉ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ውስጥ ከ96 በመቶ በላይ የሚሆነው ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚመነጭ ሲሆን፤ ይህም ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ በአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት ቀዳሚ እንድትሆን አስችሏታል፡፡

ይህ አስተማማኝና ንጹህ የኃይል አቅርቦት መፈጠሩ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለማሻሻል፣ አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅ እንዲሁም አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመፍጠር የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን ነው።

ኢትዮጵያ ይህንን ንጹህ ኃይል ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማቅረብ ባለፈ ለጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በመሸጥ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን እንዲሁም አረንጓዴ ልማትን በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ሆናለች፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ