አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት የዲፕሎማሲ ጥረት በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊቆሙ ይገባል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፡፡
ነዋሪዎቹ ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በውስጥ ባንዳዎች እና በውጭ ባዕዳን ፖለቲካዊ ሴራ ያጣነውን የባሕር በር ለማግኘት መንግሥት የጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሀብቴ÷ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባሕር በር ባለቤትነቷን ያጣችበት መንገድ የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እያደገ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የሕዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ የባሕር በር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ሆኖ መቅረቡ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት በመሆኗ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖዎች እየተጋለጠች እንደምትገኝ ጠቁመው÷ የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪነትና ቀጣናዊ መሪነቷን ለማጠናከር የባሕር በር አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ደጄኔ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድ ፍትሃዊ አይደለም፤ ስለሆነም በዲፕሎማሲና በንግግር ጥያቄው መልስ እንዲያገኝ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የባሕር በር ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ከሚያከናውነው የዲፕሎማሲ ጥረት በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ለብሔራዊ ጥቅማቸው በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የባሕር በር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ከማሳለጥ ባለፈ ወጣቶች በባሕር ትራንስፖርት ዘርፍ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ያስችላል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ባንጃው ታደሰ ናቸው፡፡
የወጪ ንግድን በማፋጠን ለምርት የሚሆኑ ግብዓቶችን እና የፍጆታ ዕቃዎችን ያለ እንከን በማስገባት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
ነዋሪዎቹ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ በመሆኑ ጥያቄው እንዲመለስ በትብብር እና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ