አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ቱሪዝምን እንደ አንድ የኢኮኖሚ እድገት ዋና አንቀሳቃሽ አድርጎ በመውሰድ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን አድርጓል።
በርካታ ማህበራዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በማልማት የቱሪዝም ዘርፉ የአቅሙን ያህል ለሀገር ኢኮኖሚ አበርክቶ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተተገበሩት ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ገፅታ በመገንባትና የቱሪዝም ፍሰቱን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው፡፡
አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከል ብቻ ሳይሆን፤ ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በተወጠነው የገበታ ለሸገር መርሐ ግብር በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተገንብተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የተገነቡት የወዳጅነት፣ አንድነትና እንጦጦ ፓርኮች ከወንዝ ዳር ልማት ስራዎች ጋር ተዳምረው ከተማዋን የውበት ሸማ ከማልበሳቸውም በላይ የኮንፈረንስና የከተማ ቱሪዝምን አሳድገውታል።
ገበታ ለሀገር የቱሪዝም ልማትን ወደ ክልሎች በማስፋት የተከወነ ትልቅ ስራ ሲሆን፤ ወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት ተከናውኗል፡፡
እነዚህ ስራዎች አዳዲስ ዘመናዊ የመዝናኛ ስፍራዎችን በመገንባትና የተፈጥሮ ሀብት እያላቸው ነገር ግን የመሰረተ ልማት ክፍተት የነበረባቸውን ቦታዎች ወደ ዘመናዊ መዳረሻነት በመቀየር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ሌላኛው ደግሞ ገበታ ለትውልድ ሲሆን፤ በዚህ ስር በቅርቡ ተመርቆ ወደ ስራ የገባው የአርባ ምንጭ ኮንፍረንስ ሪዞርትን ጨምሮ ሎጎ ሀይቅ ሪዞርት፣ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ እና ሸበሌ ሪዞርት ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች የተፈጥሮ ጥበቃን ከዘመናዊ እንግዳ መስተንግዶ ጋር ያጣመሩ ናቸው፡፡
እነዚህ ስራዎች ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ የቱሪዝም ሀብት የመፍጠር አላማ ያላቸው ናቸው።
በዚህም ቀደም ሲል በውጭ ዜጎች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረውን ዘርፍ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውንና ባህላቸውን እንዲጎበኙ በማድረግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን አነቃቅቷል።
በተጨማሪም በፕሮጀክቶቹ ግንባታና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ለብዙ ሺህ ወጣቶች የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን፤ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከማሳደግ ባሻገር የከተሞችን ውበትና ንፅህና በመጠበቅ የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ እንዲረዝም አድርገዋል።
በአጠቃላይ በመደመር መንግሥት እይታ የተቀረጹት የገበታ ለሸገር፣ ለሀገር እና ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ያልተነካ ሀብት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም በመቀየር ሀገሪቱን ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጠኑ ናቸው።
በመልካም ፈቃዱ