አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ባለፉት ዓመታት ከነዳጅ ዋጋ መናር እስከ ኮቪድ-19 ወረርሽኝና የጂኦፖለቲካ ውጥረቶችን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን አስተናግዷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች መሃል ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር በአህጉሪቱ ያለውን የበላይነትና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነት ማስቀጠል ችሏል።
አየር መንገዱ በመደመር መንግሥት ቁርጠኛ አመራር ከዘመናዊ አውሮፕላኖች ግዥ እስከ ሜጋ ኤርፖርት ግንባታ፤ ከበራራ ማሰልጠኛ እስከ ጥገና ማዕከላት ማስፋፋት ባከናወናቸው የልማት ሥራዎች ጉዞውን አፋጥኗል።
አየር መንገዱ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ለማሳደግና ለማዘመን ባለፉት ስምንት ዓመታት ታሪካዊ የተባሉ የዘመናዊ አውሮፕላኖች ግዥ ስምምነቶችን ፈጽሟል።
በዚህም 74 አዳዲስ አውሮፕላኖች ገዝቶ ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን፤ 117 አውሮፕላኖች ለመግዛት ከቦይንግ እና ኤርባስ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ፈፅሟል፡፡
እነዚህ ስምምነቶች 80 ዓመት ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ 787 ድሪምላይነር፣ 737 ማክስ፣ ኤ350-900 እና ኤ 350-100 የመሳሰሉ ዘመናዊ፣ ነዳጅ ቆጣቢና የአካባቢ ብክለትን ያገናዘቡ አውሮፕላኖች ባለቤት እንዲሆን ያስችሉታል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጠቀማቸው አውሮፕላኖች አማካይ እድሜ 9 ነጥብ 3 ዓመት ሲሆን፤ ይህም የሚጠቀማቸው አውሮፕላኖች አዳዲስ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
የዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎቹን በከፍተኛ ደረጃ ያሳደገው አየር መንገዱ፤ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ብቻ በአራት አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የበረራ አገልግሎት ጀምሯል፡፡
በዚህም የዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ቁጥር ወደ 150 ያደረሰ ሲሆን፤ በሀገር ውስጥ ነገሌ ቦረና፣ ጎሬ መቱ እና ደብረ ማርቆስን ጨምሮ አዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎችን በመገንባት በረራ ጀምሯል፡፡
ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅም በላይ እየሆነ የመጣውን መንገደኞች ቁጥር ለማስተናገድ ያለመው ግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በይፋ መጀመሩም ይታወሳል፡፡
12 ነጥ 5 ቢሊየን ዶላር ወጪ የሚገነባው ይህ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት እስከ 100 ሚሊየን ተሳፋሪዎችን የማስተናገድ አቅም የሚያስተናግድ ሲሆን፤ የአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ማዕከል ለመሆን ያስችላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ ዓላማን ያነገበ ነው።
በተጨማሪም የቀደመውን የአብራሪዎችና የቴክኒሺያኖች አካዳሚ ወደ ኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲነት በማሳደግ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ተማሪዎች ሥልጠናዎችን በመስጠት ከአህጉሪቱ ቀዳሚ የአቪዬሽን የትምህርት ማዕከል ፈጥሯል።
አየር መንገዱ በፋይናንስ ረገድ አስደናቂ ስኬትን ያስመዘገበ ሲሆን፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ የ20 በመቶ ዕድገት በማሳየት 9 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
በዚህ ዓመት ብቻ 20 ነጥብ 7 ሚሊየን ተሳፋሪዎችን እና 897 ሺህ ቶን ጭነት ማጓጓዝ ችሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 8 ዓመታት ያስመዘገባቸው ደማቅ ስኬቶች የቪዥን 2035 ስትራቴጂውን ዕውን ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት ወሳኝ ርምጃ ናቸው፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ