የሀገር ውስጥ ዜና

ምክክሩ በሰላማዊ መንገድ የተሻለች ሀገር የመገንባት ዓላማን ያነገበ ነው – ተመካካሪዎች

By Yonas Getnet

August 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ በሰላማዊ መንገድ የተሻለች ሀገር የመገንባት ዓላማን ያነገበ ሂደት ነው አሉ ተመካካሪዎች፡፡

በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች በሀገሪቱ ያሉ ችግሮችን በውይይትና በመግባባት ለመፍታት እየተካሄደ ያለው ሂደት ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመካካሪዎቹ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ በጦርነትና በጥላቻ ሳይሆን በውይይት ችግሮችን የመፍታት፣ ሰላማዊና ጤናማ ሀገር የመገንባት ዓላማን ያነገበ ሂደት ነው።

በምክክሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ አካላት የተወጣጡ ተሳታፊዎች በእኩልነት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሂደቱ ከትንንሽ ቡድኖች ውይይት በመነሳት ወደ ሰፋፊ የምክክር መድረኮች መሸጋገሩን አንስተው፤ በዚህም ተሳታፊዎች የሌሎች ማህበረሰቦችን ችግሮችና እይታዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

የሚነሱ ሀሳቦች ለሀገር ያላቸው ጥቅምና ጉዳት በጋራ እየተመዘነ ወደ የጋራ መግባባት ለመድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ምክክሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ሰዎች ተሞክሯቸውንና ችግሮቻቸውን በቀጥታ የሚያካፍሉበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን በአንድ መድረክ ተቀምጠው የተለያዩ ህመሞችንና ችግሮችን በመወያየት የጋራ መፍትሔ መፈለጋቸው ለዘላቂ ሰላምና መግባባት ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት