አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ዋነኛ ኃላፊነት የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር፣ የህዝቦችን አብሮ የመኖር አንድነት ማጠናከር እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማፋጠን ነው፡፡
ነገር ግን በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የሕገ ወጡ ህወሓት ጉዞ ከዚህ እሳቤ የወጣና ለሀገር ቀጥተኛ ህልውና አደጋ የደቀነ መስመር ሲከተል መቆየቱን በርካታ የታሪክና የፖለቲካ ተንታኞች ይስማሙበታል።
ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተከተለው የፖለቲካ አካሄድ የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት ከማጎልበት ይልቅ ልዩነቶችን በማስፋት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
የቀድሞ የህወሓት መስራች የነበሩት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፖለቲካዊ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቡድኑ በ1968 ዓ.ም ባወጣው ማኒፌስቶ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር መካዱንና ታሪኳን የሚያናንቅ አቅጣጫ በግልጽ አስቀምጧል።
ከትጥቅ ትግል ዘመን ጀምሮ የራሱን ጠባብ የቡድን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲልም ከውጭ ጠላቶች ጋር ህብረት በመፍጠር ሀገር የማፍረስ እና የባንዳት ተልዕኮውን ሲወጣ መቆየቱንም አብራርቷል።
በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚገባው ህገ ወጡ ቡድን ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት የነበራትን የባህር በር እንድታጣ በማድረግ ረገድ ታሪካዊ ክህደት ፈፅሟል፡፡
የህገ ወጡን ቡድን አሁናዊ እንቅስቃሴን በተመለከተ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)ድርጅቱ ስለ ሀገር እንደማይጨነቅና ኢትዮጵያ ብትፈርስ ደንታ እንደሌለው ያስረዳሉ።
ሌላኛው የቀድሞ የህወሓት መስራች ገብሩ አስራት ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ ፍርሃትንና ሽብርን በመንዛት ሴቶችን፣ ወጣቶችንና አረጋውያንን እያሰረ እና እያሳደደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህም ድርጅቱ ከአምባገነንነት አልፎ ሙሉ በሙሉ ወደ ሽብርተኝነት መሸጋገሩን የሚያሳይ መሆኑን የድርጅቱ መስራች ያብራራሉ።
ህገ ወጥ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ራሱን እንደ መንግሥት በመቁጠር ራሱ ያጸደቀውን ሕገ መንግሥት እና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሻረክ ቀጣናውን ወደ አዲስ የጦርነት አዙሪት ለማስገባት እየሰራ መሆኑንም ነው የሚያስረዱት።
በ2010 ዓ.ም የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ያጣውን የስልጣን ወንበር ለመመለስ ሲል ቡድኑ ለበርካታ ዓመታት ህዝብንና ድንበርን ሲጠብቅ የነበረውን የሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባ በመውጋት የሀገር ክህደት ፈጽሟል።
ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው ዓመታት ሀገራዊ አንድነትን ከመገንባት ይልቅ ህዝብን በብሔር እና በቋንቋ በመክፋፈል ሀገርን አደጋ ላይ ጥሎ አልፏል።
በመሆኑም ይህን ሀገር አፍራሽ እሳቤ እና ከጀርባው የተዘረጋውን የውጭ ኃይሎች የጥፋት ገመድ በሀገራዊ አንድነትና በጸና ሉዓላዊነት መመከት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
በዮናስ ጌትነት