የግብርና-ምግብ ሥርዓትን መቀየር ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን፣ የተቀናጀ የክፍለ አህጉር ርምጃዎችን እና የኢንቨስትመንት ዕድገትን የሚጠይቅ ነው አለ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)፡፡
የአፍሪካን አዲስ የጸና እና ቀጣይነት ያለው የግብርና-ምግብ ስርዓት ማዕቀፍ ትግበራ ለማፋጠን በአዲስ አበባ ከፍተኛ ደረጃ የመማማሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የሁለት ቀናት መድረኩ የኢጋድ አምባሳደሮች ኮሚቴን፣ የኢጋድ የግብርና-ምግብ ስርዓት ፓርላማ መድረክን፣ የብሔራዊ CAADP የትኩረት ነጥቦችን እና ቴክኒካዊ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ የክፍለ አህጉሩን ሂደት ለመገምገም ያለመ ነው፡፡
እንዲሁም የካምፓላ መግለጫን እና የ2026–2035 ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብር ባለቤትነትን ለማጠናከር ያለመ ነው።
የኢጋድ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር መሐመድ ኦመር ዲጃማ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የግብርና-ምግብ ስርዓት ለውጥ በክልሉ ኢኮኖሚ፣ ማህበረሰብ፣ ፖለቲካዊ መረጋጋት እና ክልላዊ ውህደት ላይ ጉልህ ፋይዳ አለው፡፡
ቀጣይነት ያለው የምግብ ዋስትና እጦት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት እና ዝቅተኛ ምርታማነት የግብርና-ምግብ ስርዓት ለውጥን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ክልላዊ ውህደትን የሚያረጋግጥ አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
የክልል ቁርጠኝነትን ወደ ተግባር ለመለወጥ የፓርላማዎች እና የዲፕሎማሲ ተቋማት እርስ በእርስ የሚደጋገፉ ሚናዎች ወሳኝ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም የፓርላማ አባላት ህጎችን በመቅረጽ፣ ብሔራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች እና በጀቶችን በመወሰን ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአምባሳደሮች ኮሚቴ ደግሞ ስትራቴጂካዊ ፖለቲካዊ መሪነት ይሰጣል ብለዋል።
የኢጋድ አምባሳደሮች ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር መሐመድ አሊ ሀሰን÷ የካምፓላ መግለጫን ለማራመድ ኮሚቴው ያላውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
አባል ሀገራት የምግብ ዋስትናን እና የግብርና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያን ወክሎ የተናገረው የፓርላማው የግብርና ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሶሎሞን ላሌ÷ ሀገሪቱ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ያካበተችውን ልምድ እና የጋራ የክልል ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የፓርላማ ተሳትፎ ያለውን ፋይዳ አንስቷል።
የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እና በክረምት ወራት የሚከናወነውን ሰፊ የስንዴ መስኖ ልማት በማሳያነት የጠቀሱት አቶ ሶሎሞን፣ በኢነርጂ፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ እና በማዳበሪያ ምርት ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ላይ የተደረጉ ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን ጠቁመዋል።
የኢጋድ ሀገራት ድህነትን፣ የምግብ ዋስትና እጦትን እና ሰላም እና መረጋጋትን የሚፈታተኑ የጋራ ችግሮች እንዳሉባቸው የገለጹት ሰብሳቢው፣ እነዚህን ለመቅረፍ ጠንካራ አንድነት፣ የተቀናጀ ርምጃ እና የጋራ ዓላማ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢጋድ የኢኮኖሚ ትብብር እና ክልላዊ ውህደት ዳይሬክተር ዶ/ር መሂይኤልዲን ኤልቶአህሚ ከተለመደው የግብርና ዕድገት ወጥቶ ምርትን፣ ንግድን፣ የአየር ንብረት መቋቋምን እና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን የሚያጠቃልል ሰፊ የግብርና-ምግብ ስርዓት አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የፖሊሲ ተቋማት እና የፓርላማ አባላት የካምፓላ ማዕቀፍን ተግባራዊ ለማድረግ፣ በተለይም አዲስ በተቋቋመው የኢጋድ የግብርና-ምግብ ስርዓት ፓርላማ መድረክ በኩል የማይተኩ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።