አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ አውዳችን ከተቃርኖ ስሜት ወጥቶ በይቅርታ ጎዳና እንዲራመድ መሰረት የጣለ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የሀገር ብርታት፣ ጥበብና ብልሃቱ በሰለጠነ መንገድ ልዩነትን በምክክር መፍታት ነው፡፡
የዛሬዋ ዕለት ድምቀቷና ቁም ነገሯ ለሀገር የሚበጅ፣ ለትውልድ የሚዋጅ እና አንድነታችንን የሚያጸና የጋራ መሻትና መልካም ተስፋችን የተገለጠባት በመሆኗ ልዩ ቀን ነች ብለዋል፡፡
ይህን ከፍ ያለ ሃላፊነት ተቀብለው ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለኮሚሽኑ አመራሮች፣ ሰራተኞች፣ ተመካካሪዎች እና ሌሎች አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎች በምክክራችሁ የነገን እንድንመለከት የሚያስችለን የህብር ድምጻችንን ስላሳያችሁን እናመሰግናለን ነው ያሉት፡፡
ለኢትዮጵያ እድገቷና ግስጋሴ መሰረት የሆኑትን የጋራ ሐቆች ናቸው ብላችሁ ምክረ ሃሳቦችን አዘጋጅታችሁ በማቅረባችሁ ታሪካዊ ስኬት ነውና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በሒደታችሁ እውንም ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ የሚሻገር አሻራ አስቀምጣችኋል ሲሉም አወድሰዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ የኢትዮጵያ ነባር ባህል የሆነውን ምክክር እውን ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ለተጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክሩ የቀረቡ ሃሳቦች ለፖለቲካ ልምምዳችን እና ለሀገር ግንባታ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመከባበርና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተጠናቀቀው የምክክር ጉባዔ በሰከነ መንፈስ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል አዲስ ባህል የፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ