አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በዛሬው እለት በስኬት ተጠናቅቋ አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ስላሴ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በዚህ ታሪካዊ መድረክ 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ በመሰባሰብ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሲመካካሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ተመካካሪዎቹ በመጨረሻም ለዘመናት ለቆዩ አለመግባባቶች መፍትሄ የሚሆኑ ምክረሃሳቦችን አጠናቅረው ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሂደቱ ተመካካሪዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በቀላሉ እየተግባቡ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ጊዜ ወስደው ጠንከር ያሉ ውይይቶችን እያደረጉ በመጨረሻም በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ሂደቱን ሲከታተል ሁሉም የምክክር መድረኮች በመደማማጥ፣ በመከባባር እና በመቻቻል ሲከናወኑ እንደነበር ማረጋገጥ እንደቻለም ነው የገለጹት፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ልዩነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ተወያይተው የጋራ መግባባት በመፍጠር በጋራ ወደፊት መራመድ የሚችሉበትን እድል መፍጠር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክር አሸናፊና ተሸናፊን የመለየት ሂደት አይደለም ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ይህ ሂደት አንዱ ወገን ተሸንፎ ሌላው ወገን የሚያሸንፍበት ውድድርም አይደለም ብለዋል።
እንደ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገለፃ በዚህ የምክክር ሂደት ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ ተዋውቀዋል፣ ጠንካራ ግንኙነቶችን ፈጥረዋል፣ የተለያዩ አመለካከቶችን አዳምጠዋል፣ እንዲሁም የሀገራችንን ፈተናዎች በተመለከተ ሃሳቦችን ተለዋውጠዋል፤ በመጨረሻም መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
ይህ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያሉባትን የሃሳብ ልዩነቶች በምክክር መፍታት መቻሏን ያሳየችበት ታሪካዊ ምእራፍ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡