አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘመናትን የተሻገሩ የውስጥ ቁርሾዎችንና ሀገርን ዋጋ ያስከፈሉ ውስብስብ አገራዊ ፈተናዎችን በሰለጠነ ውይይት የመፍታት ጥበብ የኢትዮጵያ አዲሱ የከፍታ መገለጫ ሆኖ ተመዝግቧል።
ላለፉት አርባ ቀናት ሲካሄድ የቆየውና በትናንትናው ዕለት በስኬት የተቋጨውን ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላምና የመንግስት ግንባታ ሂደት በጥንካሬ ከማንበሩ ባሻገር ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሚሆን ታላቅ ተግባር ሆኖ አልፏል።
ይህ “እንችላለን” በሚል ቁርጠኝነት የተመራ መድረክ በራሷ ልጆች ጥረትና አቅም የተከናወነ ከመሆኑም በላይ፣ በውይይት ባህል ችግርን የመፍታት ሂደትን ለአህጉሪቱ በተግባር ያስመሰከረ አዲስ ምዕራፍ ነው።
በማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ኢትዮጵያውያን በሌላ ታላቅ አሸናፊነት ለአህጉሩ አምባሳደርና ምሳሌ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከአራት ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ያቀፈው ይህ አካታች የምክክር መድረክ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር ጽኑ መሠረት የጣለ መሆኑን ያብራሩት ኦባሳንጆ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢኮኖሚ እድገት ሰላሟን በማስጠበቅ ከቀጠለች በአፍሪካ ትልቁን ኢኮኖሚ የመያዝ ብቻ ሳይሆን ካደጉ የዓለም ሀገራት ተርታ እንደምትሰለፍ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ይህም የውስጥ ችግርን በስኬት በራስ የመፍታት አቅም ለመላው አፍሪካውያን ትልቅ ትምህርት ይሆናልም ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ለአፍሪካውያን የጽናትና የጀግንነት ተምሳሌት መሆኗን አውስተዋል።
የዓድዋ ድል የአውሮፓውያንን የበላይነት ትርክት ያከሸፈና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ብስራት መሆኑን የጠቀሱት ኬንያታ አዲስ አበባ የአፍሪካዊያን አንድነት መሰረት የተጣለባት መሆኗን አስታውሰዋል።
አሁንም የተጠናቀቀው የምክክር ምዕራፍ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን እንደገና ያበረከተችው ታላቅ የሰላም ስጦታ መሆኑን በመጠቆም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲቆሙ፣ እርስ በእርስ እንዲታረቁ እና ዘላቂ የሰላም ውርስ እንዲያቆዩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ይህ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅምና በሰለጠነ ውይይት ፈትተው ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ መሸጋገር እንደሚችሉ ያሳየ፣ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሚሆን ታሪካዊ የድል ምዕራፍ ነው።
የቀደመውን የጀግንነትና የጽናት ታሪክ ከአሁኑ የልማትና የሰላም ጥረት ጋር በማስተሳሰር ኢትዮጵያ ራሷን አሻግራ ለመላው አፍሪካውያን የተስፋ ብርሃን የመሆን ታሪካዊ ተልዕኮዋን በጽናት እየተወጣች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ያሳየችው ይህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት ልክ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ለአፍሪካ የሚተርፍ የሰላም ውርስ ሆኖ ይቀጥላል።
በዮናስ ጌትነት