አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ምሳሌ፣ የነጻነት ምልክት እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆን የአፍሪካ እናትነቷን በተግባር ያሳየች ሀገር ናት፡፡
ይህ እውነት ከኢትዮጵያውያን ባለፈ በተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች እና የታሪክ ተመራማሪዎች እውቅና ሲያገኝ ደግሞ የኢትዮጵያን አህጉራዊ መሪነት ሚና ይበልጥ ያጠናክረዋል፡፡
የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማጠቃለያ ላይ ያደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያ አሁንም የአፍሪካ እናት መሆኗን እና የአህጉሪቱ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ኬንያታ በንግግራቸው ኢትዮጵያ መላው አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ስር በወደቁበት ዘመን የጣሊያንን ወረራ በመቀልበስ ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ የነፃነት ቀንዲል ያበራች ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡
ዓድዋ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ እና የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ነው ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ÷ ድሉ አፍሪካውያን ለክብራቸው እና ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ሞራል የሰጠ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከበርካታ ዓመታት በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በአፍሪካ ውስጥ ተከፋፍሎ የነበረውን የፖለቲካ ልዩነት በማስታረቅ በፈረንጆቹ 1963 የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም አፄ ኃይለ ሥላሴ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያውያን እና የአፍሪካውያን ነፃነት እና ክብር እንዲጠበቅ አጥብቀው መሞገታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ፣ መግቢያ በር እና የፖለቲካ ማዕከል መሆኗን አውስተው ÷ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲና ጭምር ናት ብለዋል፡፡
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት በውስጥ እና በውጭ ችግሮች ሲያጋጥሟት መቆየቷን የተናገሩት ኡሁሩ ኬንያታ÷ ነገር ግን ሁሉንም ተግዳሮቶች አልፋ እንደ ሀገር መፅናት ችላለች ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የተደረገውን ጥረት አድንቀው÷ ምክክሩ ሀገርን ለማፅናት እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን አፍሪካ ሰላም ትሆናለች፤ ድንበር ዘለል ንግድና እና ቀጣናዊ ትስስሮች ይጠናከራሉ፤ ይህም የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ እድገት እንዲሳለጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔን እንከተል ያልነው አፍሪካውያን ችግራቸውን በምክክር እና በሽምግልና የመፍታት የቆየ ባሕል ስላላቸው ነው ብለዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች በራሷ እና በአፍሪካውያን ትብብር ለመፍታት ሁሉም ያሸነፈበትን የምክክር ጉባዔ በስኬት አጠናቅቃለች፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ ለዘመናት የዝግ የነበረው ልዩነትን በውይይት የመፍታት ልማድ የተቀየረ ሲሆን ÷ በተካሄደው አካታች ሀገራዊ ምክክርም ሰፊው ሕዝብ የውሳኔው ቀጥተኛ ባለቤት የሚሆንበት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።
የምክክር ሒደቱም ኢትዮጵያ እንደተለመደው ያሸነፈችበት እና የታሪካዊ ጠላቶችን ቅስም የሰበረችበት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ