የሀገር ውስጥ ዜና

የመደመር መንግሥት የፕሮጀክት አፈጻጸም ባህል ማሳያ – መገጭ

By Hailemaryam Tegegn

August 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች “ሞቷል” እስኪባል ድረስ ቆሞ የነበረው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገለት ከፍተኛ ክትትልና ርብርብ ለትንሳኤው ቀርቧል፡፡

የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ባለፈ በተያዘላቸው ጊዜ በሚፈለገው ጥራት የማጠናቀቅ ባህል እንዲዳብር ያስቻሉ በርካታ የልማት ሥራዎችን ሲከውን ቆይቷል፡፡

ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች ባለፈ ለበርካታ ዓመታት የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ሂደት በመገምገም ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ ይገኛል፡፡

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የመገጭ ግድብ ግንባታ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገለት ከፍተኛ ክትትልና ርብርብ አፈጻጸሙ 94 በመቶ መድረሱ ተገልጿል፡፡

የግድቡ ሥራ በአሁኑ ወቅት ጥራቱን ጠብቆ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይ ጥቂት ወራት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ፅ/ቤት ስራ አስኪያጅ አሸናፊ ሊካሳ እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ ለበርካታ ዓመታት በኮንትራክተር አቅም ማነስና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት “ሞቷል” እስኪባል ድረስ ቆሞ የነበረ ነው።

ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀጥተኛ ትዕዛዝ አማካኝነት፤ የአቅም ችግር የነበረበት የቀድሞው ኮንትራክተር በአዲስ በመተካቱ ፕሮጀክቱ ዳግም ትንሳኤ አግኝቶ ወደ ስኬት ጎዳና ሊመለስ ችሏል።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ የመስኖ ውሃ መቆጣጠሪያ ግንባታ እንዲሁም ተያያዥ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችም መጠናቀቃቸው ነው የተገለጸው፡፡

ግድቡ አሁን ላይ 33 ሚሊየን ሜትር ኪውብ ውሃ የያዘ ሲሆን፤ በተገነቡት የመስኖ ውሃ መውጫዎች አማካኝነት በቀን 5 ሚሊየን ሜትር ኪውብ ውሃ መውጣት ጀምሯል፡፡

ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የንፁህ መጠጥ ውሃ የመስመር ዝርጋታ ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፤ የውሃ ማማ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውም በመጠናቀቅ ላይ ነው።

የማጠናቀቂያ ስራዎቹ በጥሩ ሁኔታ እየተገባደዱ መሆኑን የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ አሁን የሚቀረው የ6 በመቶ ስራ ብቻ በመሆኑ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አረጋግጠዋል።

የመገጭ ግድብ ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፤ በተጨማሪም የጎንደር ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደሚቀርፍ ይጠበቃል።

በዓለምሰገድ አሳዬ