አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በመሠረታዊ የጤና አገልግሎት ላይ የተደረገው ኢንቨስትመንት የጤና አገልግሎቶችን ወደ ማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሚሊዮኖችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ጉባኤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በአፍሪካ የጤና ሥርዓትን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የሀገራትን ስትራቴጂካዊ ትብብር የበለጠ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካ የዜጎቿን የጤና አጠባበቅ ስርዓት በማዘመን በተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ሁኔታ የሚደርስን የጤና ተጋላጭነት በራስ አቅም ምላሽ መስጠት አለባት ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ እነዚህ ተግዳሮቶች አፍሪካ ቀጣናዊ ትብብር ውስጥ የጋራ ድምጿን ለማጠናከርና በጤና ጉዳዮቿ ላይ ሙሉ ባለቤትነትን ለመያዝ ታሪካዊ ዕድል ይፈጥራሉ ነው ያሉት።
አፍሪካ በግልጽና በደፋር አቅጣጫ የተመሠረተ፣ የተቀናጀ የጋራ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልጋት ጠቁመው በጤና ላይ የምታደርገውን የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ማሳደግ እንዳለባትም አስገንዝበዋል።
የአህጉሪቷን የጤና ስርዓት ለማዘመንም ስትራቴጂክ አጋርነት በማጠናከር የጤና ደኅንነት የራስ መድኃኒቶች፣ ክትባቶችና የምርመራ መሣሪያዎችን ማምረትን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት እና በአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከያ ማዕከል መካከል ተግባራዊ ቅንጅት ማጠናከር ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ግብ ጋር አቆራኝቶ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ጤናን እንደ ስትራቴጂካዊ ብሔራዊ ኢንቨስትመንት እንደምትመለከት ገልጸው፤ ለጤና የሚመደበው በጀት በተከታታይ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎችን ቁጥር በማሳደግ የጤና ሥርዓቱን ማጠናከሯንና ይህም በእናቶች፣ ሕፃናት እና ልጆች የመኖር ዕድል ላይ ጉልህ መሻሻል እንዲመጣ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ የጤና ስጋቶችን ለመቋቋምም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሯን በማስፋት ሚሊዮኖችን በማሳተፍ በርካታ ችግኞችን ተክላለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ዘላቂ የጤና ሥርዓት ያለ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር እንደማይችል ገልጸው በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች የተሳተፉበትን አካታች ብሔራዊ ምክክር በማካሄድ ትልቅ ምዕራፍ አሳልፋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያም በብሔራዊ ኢንቨስትመንት፣ በቀጣናዊ ትብብርና ለአህጉራዊ ተቋማት በማይናወጥ ድጋፍ የራሷን ድርሻ ለመወጣት ሙሉ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።